ዕድሌ ሆኖ ወንድ አይበረክትልኝም፡፡ ወንዶች ለእኔ በአጭሩ ሳሙናዎች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይቀርባሉ፣ ነገር ግን እኔም ምስኪን ነኝ አምኜ እቀርባቸዋለሁ፡፡ እነሱም የልባቸውን ካገኙ በኋላ ‹‹ጌታ ያጣፍልሽ›› በማለት ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዴ የወንድ ልጅን ልብ ማግኘት አይቻልም እላለሁ፡፡ ስለሆነም ጥያቄዬ የወንድን ልጅ ልብ ማንበርከክና ልቡንም አግኝቶ ለማቆየት መስተፋቅር ይሻል ይሆን? በማለት ያሰብኩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ውበት ሳያንሰኝ ወንዶች እንደ ዘንድሮ መብራት ብልጭ እያሉ የሚጠፉበት ምክንያቱ ግራ አጋብቶኛል፡፡ ወይስ የ40 ቀን ዕድሌ ሆኖ ነው?
ሰብለ ነኝ
ውድ የጋዜጣችን ተከታታይ ሰብለ ጥያቄሽን በአክብሮት ተቀብለናል፡፡ በአጭሩም ጥያቄሽን እንዴት በወንዶች ተወዳጅ ለመሆን ለረጅም ጊዜ ተፈቃሪ መሆን እችላለሁ የሚል ይመስላል፡፡ በአጭሩ፡፡ ሆኖም ከጥያቄሽ እንደተረዳነው ለፍቅር ትስስርሽ ዘላቂነት አለመኖር ምክንያቱን በወንዶች ላይ በመጠምጠም አንዱ ከሌላው ይሻል ይሆናል በሚል እሳቤ መፍትሄውን ወንድ በመቀየር ላይ ያነጣጠርሽው ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ የማንኛውም ችግር መነሻ መሰረቱ ራሱ ባለቤቱ ነውና የወንዶችን ልብ ለመቀየር የራስን ልብ ከመቀየር ይጀምራልና ችግሩ የወንዶቹ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ያንቺ ነውና ወደ ራስሽ ተመልከች እላለሁ፡፡ የራስሽን ባህሪ ገምግሚ፡፡ ምን አይነት ባህሪሽ ደካማ እንደሆነና ወንዶችም በተደጋጋሚ የሚነግሩሽ የቱ እንደሆነ በማወቅ ለማረም ሞክሪ፡፡
ውድ ሰብለ፡- የማማለል ጥበብ ራሱን የቻለ ልዩ ክህሎት እንደመሆኑ መጠን ጥበቡን ውጤታማ ከማድረግ አንፃር መታወቅ ያለባቸው መሰረታዊ እውቀቶች አሉ፡፡ ‹‹ማማለል›› የሚለውን ቃል ‹‹ማጥመድ›› በሚለው ቃል ብንተካው አንድ ነገር ለማጥመድ ከመዘጋጀትሽ በፊት ስለወንዱ ባህሪና የአጠማመድ ጥበቡ በቅድሚያ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ስለወንዱ ደካማ ጎንም እንዲሁ ግንዛቤ መጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህን እንግዲህ ዓሳንና የዱር እንስሳትን እንደማጥመድ ልንመስለው እንችላለን፡፡ አንቺ የምትፈልጊውን ወንድም በእጅሽ ለማስገባት መሰረታዊ ሃሳቡ ተመሳሳይ እንደመሆኑ መጠን የሚከተሉትን ዋና ዋና ጥበቦች መረዳት ያስፈልጋል፡፡
– ሕግ ማማለል በቀጥታ ሳይሆን በስሜት በኩል የሚደረግ መዘውራዊ ጥቃት፡- እንዲታወቀው የሰው ልጅ ሁለት የአዕምሮ ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም የላይኛውና ውስጠኛው በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡ የላይኛው የአዕምሯችን ክፍል የሚጠራው በግልፅ መረጃዎች ላይ በመንተራስ ቀጥተኛና ምክንያታዊ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚፈልግ፣ የሚያቅድና፣ የሚወስን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፍቅር በቀጥታ በዚህ መሰል በምክንያታዊና ሎጅክ የሚወሰን ነገር አይደለም፡፡
በመሆኑም የማማለል ጥበቦችን ልዩ የሚያደርጋቸው ይህን የአዕምሮ ክፍል በማለፍና በመዝለል በቀጥታ ወደ ውስጠኛው የአዕምሮ ክፍል ዘልቆ መግባት የሚያስችሉ መሆናቸው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ፍቅር ስሜት ነው፡፡ ስሜታችን ደግሞ ያለው በውስጠኛው የአእምሯችን ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ይህን ክፍል ለመነካካትም አቋራጭ መላ ወንዶችን በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መቅረቡ ላይ ነው፡፡ የቀጥታ ቀረቤታ ብዙ ጊዜ አዋጭ አይደለም፡፡
ሕግ 2 ፍቅር ሃሳብ መሆኑን እወቂ፡- ስለ አንድ ነገር የበለጠ በታሰበ ቁጥር ለዚያ ነገር የሚኖረን ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ለአንድ ነገር የሚኖረንን ፍላጎት፣ የውሳኔና ድርጊት የበለጠ ለመጨመር ከተፈለገ ለዚያ ነገር የበለጠ ማሰብን ግድ ይለናል፡፡ ይህ በስነ ልቦና አጠራር ‹‹Obssesion›› የሚባለውንና አስተሳሰቡን የሚወክለውን ድርጊት ነው፡፡ የበለጠ የምናስበውን ነገር ለማድረግ እንገፋፋለን፡፡ በመሆኑም የማማለል ጥበቦች የመረጥሽውን ወንድ ፍቅረኛ የበለጠ ስለአንቺ አብዝቶ እንዲያስብ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ያደረግሻቸውን ትዝ እያለው፣ በምታደርጊያቸው ግራ እየተጋባ፣ ራሱን እየጠየቀ፣ እየተደነቀና እየተብከነከነ በሄደ ቁጥር በአንቺ ፍቅር ተይዞ ያርፈዋል፡፡ የማማለያ ቴክኒኮች እንዴት ወንድ ልጅን በፍቅር ሊያሲዙ እንደሚችሉ ስትመለከቺ ሊገርምሽ ይችላል፣ ዋናው ዘዴያቸው በዚህ ሕግ ላይ የሚሽከረከሩ መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም በተቻለ መጠን በህይወቱ ጊዜ የሌለውን ወንድ ለማማለል አትሞክሪ፡፡ ምክንያቱም ብዙ የሚያሳስባቸውና የሚጨነቅባቸው ጉዳዮች ያሉት በመሆኑ ነው፡፡ በአንፃራዊነት ጊዜ ያላቸው ወንዶች ስለ አንቺ አብዝተው ለማሰብ ግን የተመቹ ናቸው፡፡
ሕግ 3 ወንዶችን በሚገባ ለማማለል የተለያዩ ብቃቶችሽ ላይ አነጣጥሪ፡- በእርግጥ አንድ ልዩ ብቃት በራሱ የወንዱን ልዩ ትኩረት ለማግኘትና ለመሳብ ያስችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ አስተማማኙና የብዙዎችን ቀልብ እንድትስቢ የሚያደርግሽ ግን ከአንድ በላይ የተለያዩ የአማላይ ሴት ባህሪያትን መካን ስትችል ነው፡፡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ያነገበ ወታደር እንዳስፈላጊነቱ መሳሪያዎችን የመጠቀም አቅምና አማራጭ ስለሚኖረው ጠላቱን በቀላሉ የማሸነፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሴቶች ወንዶች ‹‹ጠላቶቻቸውን›› በፍቅር ለማንበርከክ ሊጠቀሙትና ሊያነግቡት የሚገባው የተለያዩ የማማለያ ባህሪያትን ሊታጠቁ ይገባል፡፡ በመሆኑም አንድን ልዩ ብቃት ከሌለው ጋር በማጣመር መጠቀም ስትችዪ ነው አንቺን በተለየ ሁኔታ ተመራጭ የሚያደርግሽ፡፡ ስለሆነም ተወዳጅ ባህሪዎችሽ አብዣቸው፣ የሚነቀፉትንም ቀንሻቸው፡፡
ሕግ 4 ማማለል ስሜት የመበተን ኃይል ነው
የምትፈልጊው ወንድ አንቺን እንዲያፈቅርሽ በማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ እያንዳንዱ አቀራረብሽ የወንዱን ትኩረት የሚበትንና የአንቺን መስህብነት በአትኩሮ ውስጥ እንዲመሰጥ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም አቀራረብሽ ይህን ሕግ ሊከተል ይገባል እንጂ እንደተለመደው አይነት ተራ አቀራረብ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁልጊዜም ቢሆን ይህን መሰል መስህባዊ ገፅታን መላበስ ይጠበቅብሻል፡፡ የተፈላጊነትን ስሜትን መፍጠር፣ ትኩረትን ወዳንቺ መሳብ፣ የሚፈለጉ ነጥቦች መሆናቸውን አትርሺ፡፡ በአነጋገርሽ፣ በአለባበስሽ፣ በሽቶሽ፣ በእክብካቤሽና፣ በፈቅር ጨዋታሽ፡፡
ሕግ 5 የአማላይነት ባህሪ የሚያሳድጉሽ ነው፡- እንደሚታወቀው በተፈጥሯቸው በአንድ ወይም በሁለት ምክንያቶች ከፍተኛ የማማለል ባህሪ የተካኑ ሴቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በታሪክ ውስጥ በአማላይነታቸው የሚታወቁት ሴቶች ስለማማለል ስነ ልቦና አልተማሩም ወይም አላበቡም፡፡ ይህን ክህሎት ግን በተፈጥሯቸው የታደሉት ባህሪ ነው፡፡ የስነ ልቦናም ጥናቶች እንዳስቀመጡት ከሆነ ደግሞ የትኛውንም ባህሪ በአዲስ መልክ መካን ይቻላል፡፡ የግድ በተፈጥሮ ላንታደለው እንችላለን፡፡ ማዳበር የምንፈልገውን ባህሪ ግን ደጋግሞ በመተግበር የራሳችን እንዲሆን ልናደርገውና እንደውም ተፈጥሯዊ መለያችን እስኪመስል ድረስ ከእኛ ጋር እንዲኖርና እንዲንፀባረቅ ልናደርገው እንችላለን፡፡ በመሆኑም ዕድሜ ልክሽን በወንዱ ልብ ውስጥ በፍቅር ለመቀጠል ማድረግ ያለብሽ ነገር ቢኖር የማማለያ ጥበቦቹን ደጋግመሽ በመለማመድ በዘለቄታዊነት ባህሪሽ እንዲሆኑ ማድረግ ትችያለሽ፡፡ አንድ እውቀት ወደባህሪ ደረጃ የሚዳብረውና አብሮሽም ሊቆይ የሚችለው እውቀቱን በተግባር ደጋግመሽ ስትለማመጂው መሆኑን ማወቅ ይኖርብሻል፡፡ ልክ አሪፍ የውሃ ዋና ብቃት ይኖርሽ ዘንድ ደጋግመሽ መዋኘት እንደመኖርብሽ ሁሉ የማማለል ብቃትም ከዚሁ ጋር ይመሳሰላል፡፡
ሕግ 6 ሁሉም ወንዶች ሊያፈቅሩሽ አይችሉምና አትጨነቂ፡- በእርግጥ የተለያዩ የአማላይነት ብቃቶችን በተላበስሽ ቁጥር ትኩረትን የመሳብና ፍላጎትን ወዳንቺ የመግዛት አቅምሽና አድማስሽ መስፋቱ አይቀርም፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም ወንዶች ማማለል ትችያለሽ ማለት ግን አይደለም፡፡ የምትፈልጊውን አይነት ወንድ መርጠሽ ነገር ግን በአንቺ ፍላጎት ባያድርበት ልትጨነቂ አይገባም፡፡ አማላይነትሽ በሁሉም ወንዶች ላይ ሁልጊዜ ላይሰራ ይችላል፡፡ አንቺም ራስሽ የሁሉንም አይነት ወንዶች አትኩሮትና ምርጫ ማሳካት አይጠበቅብሽምም፡፡ አንዳንድ ወንዶች እንደውም ጭራሽ ለሴት ልጅ ፍላጎት የሌላቸውም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ሕግ 7 ዋናው ነገር ልዩነት መፍጠርሽ ነው፡- በዓለማችን ላይ የተለያዩ ልዩ ተመራጭ ብቃት ያላቸውን እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሴቶች መኖራቸውን መርሳት የለብሽም፡፡ ፍቅር በምንልበት ጊዜ እንግዲህ ውድድር መሆኑንም መርሳት የለብሽ፡፡ ከብዙሃኑ ጎራ በወንዶች ዓይን ልብ ውስጥ በአንፃራዊነት የተሻለች ሴት መሆን ይጠበቅብሻል፡፡ ይህ ደግሞ ከሌሎች ተወዳዳሪ ሴቶች ወይም እሱ ከሚቀርባቸው ሴቶች ወይም ከአሁን ቀደም ከሚያውቃቸው ሴቶች የበለጠ ተመራጭ ለመሆንና ተመራጭነታችሽም ቀጣይነት ያለው ይሆን ዘንድ ከአንድ በላይ ልዩ የሚያደርጉሽ አማላይ ባህሪያትን መካን ይጠበቅብሻል፡፡
ከዚህ ህግ ውስጥ ማወቅ ያለብሽ ልዩነትሽ ላይ ማነጣጠሩ ላይ ነው፡፡ እናም አንቺ ማለት ከአንድ ወይም ሁለት ተመራጭነት በላይ ልዩ የሚያደርጉሽን ነገሮች ማብዛቱ ላይ ነው፡፡ ከተወዳዳሪዎችሽ ምንጊዜም ልቀሽ እንትታይና ልትገኝ የሚያደርግሽ፡፡ በየጊዜው ልዩ የሚያደርጉሽን አዳዲስ ተጨማሪ ነገሮች ማሳደግ ይጠበቅብሻል፡፡ በዚህ ተለዋዋጭና እያደገ በሚሄድ አማላይ ዓለም ውስጥ አንቺም ልዩ ልዩ ባህሪያትሽን እያሳደግሽና መለወጥ ያለበትንም ሁሉ በተሻለ ነገር ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብሻል እላለሁ፡፡ ዋና ዋናዎቹ መስህባዊ ኃይሎች እነዚህ ናቸውና በራስሽ ላይ ስሪ እንጂ በወንዶቹ አትማረሪ እላለሁ፤ ሰላም፡፡
The post Health: ወንዶች ለእኔ ሣሙና የሆኑበት ምስጢር የ40 ቀን ዕድሌ በመሆኑ ይሆን? appeared first on Zehabesha Amharic.