የኪንታሮት ህመም በታችኛ የትልቁ አንጀትና ፊንጥጣ አካበቢ ያሉ የደም መልስ ( veins) የደም ቧንቧዎች በሚያብጡበትና በሚቆጡበት ወቅት የሚከሰት የህመም አይነት ነዉ፡፡ የኪንታሮት ህመም ሰገራ በሚወጡበት ወቅት ሲያምጡ፣ ወይም በፊንጥጣና በታችኛዉ የትልቁ አንጀት አካበቢ ባሉ የደም ስሮች ላይ እንደ እርግዝናና ሌሎች ጭነትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች በሚኖሩበት ወቅት የሚከሰት ነዉ፡፡ ኪንታሮት በታችኛዉ የትልቁ አንጀት ዉስጥ የሚገኙ የዉስጠኛዉ ኪነታሮት (internal hemorrhoids) ወይም በፊንጥጣ ዙሪያ ባለዉ ቆዳ ስር የሚታይ የዉጨኛዉ ኪንታሮት (external hemorrhoids) አይነት በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ በሌላ በኩልም የኪንታሮት ህመም piles በመባልም ይጠራል::
የህመሙ ምልክቶች
• የኪንታሮት ህመም ምልክቶች እንደኪንታሮቱ ቦታ የሚወሰን ሲሆን የዉስጠኛዉ የኪንታሮት አይነት ብዙዉን ጊዜ በአይን የማይታይ ቢሆንም በሚፀዳዱበት ወቅት ማማጥ ካለዎ የደም ስሮቹ ሊቆጡና በቀላለ ሊደሙ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ በሚያምጡበት ወቅት የዉስጠኛዉ ኪንታሮት አይነት ወደታች በመምጣትና በፊንጥጣ ዉስጥ በማለፍ ህመምና የመቆጥቆጥ ስሜት ሊኖረዉ ይችላል፡፡
• የዉጪኛዉ የኪንታሮት አይነት በፊንጥጣ ዙሪያ ባለዉ ቆዳ ስር የሚገኝ ሲሆን የደም ስሮቹ በሚቆጡበት ወቅት ሊያሳክኩ ወይም ሊደሙ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ ደም በዉጭኛዉ ኪንታሮት ዉስጥ በመጠራቀምና በመርጋት ከፍተኛ ህመም፣ እብጠትንና መቆጣትን/መለብለብን ሊያመጣ ይችላል፡፡
• በሚፀዳዱበት ወቅት/ሰገራ በሚወጡበት ወቅት ከፊንጥጣ የሚወጣ ህመም የሌለዉ ደም/መድማት፡- ይህን ክስተት በመፀደጃ ሳህን ላይ ወይም በሶፍት ላይ ሊያዩ ይችላሉ፡፡
• በፊንጥጣ አካባቢ የማሳከክ ወይም የማቃጠል ስሜት ካለዎ
• በፊንጥጣ አካባቢ ህመም ወይም ምቾተ ያለመሰማት ካለዎ
• በፊንጥጣ ዙሪያ እብጠት ካለዎ
• የሰገራ ማምለጥ ካለዎ
የህክምና ባለሙያ ማየት የሚገባዎ መቼ ነዉ?
ምንም እንኳ ለኪንታሮት ዋነኛ ምልክቱ በሚፀዳዱበት ወቅት የደም መፍሰስ ቢሆንም በፊንጥጣ ደም መምጣት ሁሌ ከኪንታሮት ጋር ብቻ የተያዘ ሳይሆን እንደ የትልቁ አንጀት ካንሰር ወይም የፊንጥጣ ካንሰር ምልክትም ሊሆን ስለሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
• ኪንታሮት ህመም ካለዉ፣ በተደጋጋሚ ወይም በጣም የሚደማ ከሆነ፣ወይም በኪንታሮት ማስታገሻ ህመሙ የማይሻሻል ከሆነ
• ከኪንታሮት የህመም ምልክቶች ጋር አስፋልት/ሬንጅ የመሰለ ሰገራ ካለዎ፣የረጋ ደም ካለዎ፣ከሰገራዎ ጋር ደም ካዩ
• በጣም ከፍ ያለ የደም መፍሰስ ካለዎ፣ የመደበር ወይም የማዞር ስሜት ካለዎ
የኪንታሮት ምክንያቶች
ኪንታሮት በፊንጥጣ ዙሪያ ባሉ የደም መልስ ላይ ጫና በሚበዛበት ወይም በሚፈጠርበት ወቅት የደም ስሮቹ ስለሚያብጡና ስለሚወጠሩ የህመሙ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ በደም ስሮቹ ላይ ጫና እንዲጨምር ከሚያደርጉ ነገሮች ዉስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
• በሚፀዳዱበት ወቅት ማማጥ ካለ
• መፀዳጃ ላይ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ
• ተቅማጥ ወይም የሆድ ድርቀት ረዘም ላለ ጊዜ ከነበረዎ
• ውፍረት መኖር
• እርግዝና
• የፋይበር መጠናቸዉ አነስተኛ ወይም ፋይበር የሌላለቸዉን ምግቦች ማዘዉተር ናቸዉ፡፡
የኪንታሮት ህመም ጉዳቶች
• የደም ማነስ እንዲከሰት ያደርጋል
• የኪንታሮት መታነቅ/ Strangulated hemorrhoid
ሊደረጉ የሚችሉ ምርመራዎች
• የህክምና ባለሙያዎ አካላዊ ምርመራ በፊንጥጣዎ ላይ ሊያደርጉልዎ ይችላሉ
• የህክምና ባለሙያዎ የሚከተሉት ችግሮች ሊኖረዎ ይችላሉ ብለዉ ካሰቡ እንደ ኮሎንስኮፒ ያሉ ከፍ ያለ ምርመራ ሊያደርጉልዎ ይችላሉ
-ከኪንታሮቱ በተጨማሪ ሌላ የትልቁ አንጀት ችግር ይኖራል ብለዉ ካሰቡ
-ለትልቁ አንጀት ካንሰር ተጋላጭነት ካለዎ
-እድሜዎ ከ50 አመት በላይ ከሆነና በቅርቡ የኮሎንስኮፒ ምርመራ አድርገሁ የማያዉቁ ከሆነ
ለኪንታሮት ህመም ሊደረጉ የሚችሉ ህክምናዎች
ብዙዉን ጊዜ ለኪንታሮት ህምመ ሊደረጉ ከሚችሉ ህክምናዎች ዉስጥ እንደ የአኗኗር ዘይቤ ለዉጥ ያሉና እርስዎ በራስዎ ሊተገብሩት የሚችሉ እርምጃዎችን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡አንዳንዴ ደግሞ ለኪንታሮት የሚሰጡ መድሃኒቶችንና መለስተኛ የቀዶ ጥገና የህክምና ዘዴዎች ሊደረጉልዎ ይችላሉ፡፡
መድሃኒቶች
የኪንታሮት ህመምዎ መጠነኛ የሆነ ምቾት ያለመሰማት ወይም መጠነኛ ህመም ብቻ ከሆነ ያለዉ በኪንታሮቱ ላይ ሊቀቡ የሚችሉ ወይም በፊንጥጣ ሊደረጉ የሚችሉ ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድሃኒቶች ህመሙን ለተወሰነ ጊዜ ስለሚያስታግሱልዎ ገዝተሁ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የህክምና ባለሙያዎ ካላዘዘልዎ በስተቀር ያለሀኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ መድሃኒቶች እንደ የቆዳ መሳሳሰትን፣ የቆዳ መቆጣትንና ሽፍታን የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያመጡ ስለሚችሉ ከአንድ ሳምንት በላይ መጠቀም የለብዎትም፡፡
የቀዶ ጥገና፡- ኪንታሮቱን በመለስተኛ ቀዶ ጥገና ማስወገድ ወይም ኪንታሮቱን መቛጠር ሊሆን ይችላል፡፡
ሌሎች አነስተኛ የህክምና ዘዴዎች
በዉጪኛዉ የኪንታሮት አይነት ላይ የደም መርጋት ካለዎ የህክምና ባለሙያዎ የሚከተሉትን ቀላል መንገዶችን ሊተገብሩ ይችላሉ
ረበር ባንድ ላይጌሽን
ስኬሎሮቴራፒ
ኮአጉሌሽን ቴራፒ መጠቀም ይቻላል፡፡
የኑሮ ዘይቤ ለዉጥና የቤት ዉስጥ ህክምና
• ሊቀቡ የሚችሉ መድሀኒቶችን መጠቀም፡- ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ የኪንታሮት ክሬሞችን ወይም በፊንጥጣ ሊገቡ የሚችሉ መድሃኒቶችን መጠቀም
• ለብ ባለ ዉሃ ዉስጥ መዘፍዘፍ፡- በቀን ሶስት ጊዜ ለብ ባለ ዉሃ ዉስጥ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ መዘፍዘፍ
• የፊንጥጣ ንፅህናን መጠበቅ፡- በፍንጥጣ አካባቢ ያለዉን ቆዳዎትን በየቀኑ ለብ ባለ ዉሃ በመታጠብ ንፅህናዉን መጠበቅ፤ሳሙና ችግሩን ስለሚያባብሰዉ ባይጠቀሙ ይመረጣል፡፡ ከታጠቡ በኃላ ቀስ ብለሁ ማደራረቅ
• ከተፀዳዱ በኃላ ደረቅ ሶፍት ያለመጠቀም፡- ከተፀዳዱ በኃላ ሽታና አልኮሆልነት የሌለዉ የረጠበ ሶፍት መጠቀም፡፡
• በፊንጥጣዎ አካባቢ ዕብጠት ካለዎ በረዶ ወይም ቀዝቃዛ የሆነ ነገር እብጠቱ ላይ ህመሙን ለማስታገስ መያዝ
• የህመም ማስታገሻ መዉሰድ፡- ህመምዎን ለማስታገስ እንደ አሴታሚኖፌን፣አስፒሪንና አይቡፕሮፌን ያሉ የህመም ማስታገሻዎችን መዉሰድ
ብዙዉን ጊዜ በእነዚህ ህክምናዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ የኪንታሮት ህመምዎ ይቀንስልዎታል፡፡ በሳምንት ጊዜ ዉስጥ ህመምዎ ካልተሻሻለ፣ ከፍተኛ ህመም ወይም መድማት ካለዎ የህክምና ባለሙያዎን ፈጥነዉ ያማክሩ፡፡