አብዛኞቻችን አስፕሪን ከራስ ምታት ክኒንነት ያለፈ ተግባር ያለው አይመስለንም፡፡ ተከታዩ ፅሑፍ እንደሚያስረዳው ግን አስፕሪን ከራስ ምታት እስከ ስትሮክ እና ልብ ህመም ህክምና ድረስ የሚዘልቅ ከፍተኛ አገልግሎት አለው፡፡ ይህ ‹‹ተአምራዊ›› ክኒን እየተባለ የሚጠራውን መድሃኒት ሰፊ አገልግሎቶች፣ በጨጓራ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከሚመከሩት የጥንቃቄ መልዕክቶቹ ጋር የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እና ባለሞያዎችን ዋቢ አድርገን እነሆ ብለናል፡፡
የ51 ዓመቱ አቶ ሰለሞን ግርማ (ስም የተቀየረ)፣ ራሱን ሙሉ ጤነኛ አድርጎ የሚወስድና ዘወትር ስራውን በትጋት የሚሰራ፣ ከጠዋት እስከ ምሽትም ከቢሮው የማይታጣ ጠንካራ ሰው ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በቢሮው የሆነው ግን ይህን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነበር፡፡ ባላሰበው ሁኔታ እዚያው ቢሮው ውስጥ ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡ ባልደረቦቹ ተረባርበው ወደ ሆስፒታል በፍጥነት ባያደርሱት ዕድሜ ልኩን በጉት ይኖር እንደነበር አቶ ሰለሞን ያስታውሳል፡፡
አቶ ሰለሞን የገጠመው ችግር ስትሮክ ነበር፡፡ በጭንቅላት ውስጥ የደም መርጋት ወይም የደም አቅርቦት ወደ ጭንቅላት መድረስ ሲያቅተው የሚፈጠረው ይህ ችግር ብዙውን ጊዜ በግልፅ የሚታይ ምልክት ስለማይኖረው ብዙዎች ይዘናጋሉ፡፡ ታዲያ አቶ ሰለሞን በህክምና ሰዎች ከተሰጡት መድሃኒቶች አንዱ አስፕሪን ነበር፡፡ አስፕሪን ለረጅም ጊዜ እንዲወሰድ መታዘዙ ግራ ያጋባው አቶ ሰለሞን፣ የራስ ምታትና ትኩሳት እንደሌለው አንስቶ ማብራሪያ ሲጠይቅ ነበር የአስፕሪን ዘርፈ ብዙ የመድሃኒትነት ጥቅሞች የተብራሩለት፡፡ አስፕሪን እንደ አቶ አሰለሞን ላሉ ለሚሊዮኖች መድን የሆነ ዘመናትን አብሮን የኖረ መድሃኒት ነው፡፡ ጥቅሞቹ በየጊዜው እየጎሉና እየጨመሩ መምጣታቸውን ያዩ ባለሙያዎች፣ አስፕሪንን ለብዙ ችግሮች ማዘዛቸው ግን የጎንዮሽ ጉዳትን ማምጣቱ አልቀረም፡፡ ለዚህም ይመስላል የመድሃኒቱን ተአምራዊነት የሚዘረዝሩ ጥናቶች የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችንም አብረው የሚያነሱት፡፡
የአስፕሪን መነሻ
የሰው ልጆች፣ የአስፕሪን ዋነኛ ውሁድ የሆነውን ሳሊሲሌት የተሰኘ ቅመም፣ ከተለያዩ ለባህላዊ ህክምና ከሚውሉ ዛፎች ቅርፊት ላይ በመቀመም፣ ለህመም ማስታገሻነት ሲያውሉት ከ4 ሺ በላይ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የዘመናዊ ህክምና አባት የሚባለው ሂፓክራተስ ለትኩሳት እና የህመም ስሜት ለመቀነስ፣ ሳሊሲሌት የያዘ የዛፍ ቅርፊትን እንዲያኝኩ ይመክር ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወሊድ ወቅት የምጥ ህመምን ለማስታገስ ከቅርፊቱ የተፈላ ሻይ ሴቶች እንዲወስዱትም ይደረግ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በርካታ ጥረቶችና ምርምሮች ሲደረጉ ከቆዩ በኋላ በ1900 አስፕሪን በክኒን መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀረበ፡፡ ይህ የሆነው ባየር የተባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ፣ በርካታ ጥናቶች ካካሄደ እና አስፕሪን የተሰኘውን የንግድ ስም ከሰጠው በኋላ ነበር፡፡ ይህም መድሃኒቱ በባለሞያዎች በደንብ እንዲታወቅ አጋጣሚዎችን የፈጠረ ሲሆን ከ15 ዓመታት በኋላ ደግሞ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እንዲሸጥ ሲወሰን አብዛኛው ሰው፣ በቤቱ የሚያውቀውና የሚያስቀምጠው ዝነኛ ህመም አስታጋሽ ሆነ፡፡ ከህመም ማስታገስ ተግባሩ ውጪ ያሉ ዝርዝሮች እጅግም የማይታወቁ የነበረ በመሆኑ፣ በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ጥናት የሰሩ እንግሊዛዊው የፋርማሲ ባለሞያ ሮበርት ቬን እና ሳሙኤልሰን በ1982 አስፕሪንን ለዓለም እነሆ በማለታቸው የኖቤል ሽልማትን አግኝተውበታል፡፡
የአስፕሪን ሰፊ ጥቅሞች
አስፕሪን መነሻውን ከተፈጥሮ ተክሎችን ያደረገ፣ በሰውነት ውስጥ የህመም ስሜትን የሚፈጥሩ ኬሚካሎችንና ንጥረ ነገሮችን ከስርዓታችን በማገድ የእረፍት ስሜትን ይሰጣሉ፡፡ ህፃናት የህመም ስሜቶቻቸው እንዲቃለል በአነስተኛ ምጣኔ ሲሰጣቸው፣ አዋቂዎችም እንደየልካቸው ይህን የህመም ማስታገሻ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ህመምን በውጤታማነት ያስታግሳሉ፡፡
አስፕሪን ከሚሰጠው የህመም አስታጋሸነት በተጨማሪ በዋናነት የሚጠቅመው፣ የደም መርጋትን በመከላከሉ ነው፡፡ የደም መርጋት በዋናነት ስራቸውን የሚያናጋባቸው አካላት ደግሞ ልብ እና አንጎል ሲሆኑ፣ የልብ ድካም እና ስትሮክ ለገጠማቸው ሰዎች ከሚሰጡ ህክምናዎች አንዱ አስፕሪን በየቀኑ እንዲወሰዱ ማድረግ ነው፡፡ አስፕሪን እነዚህን ህመሞች ለመከላከልና ለማከም የሚረዳው፣ የደም መርጋትን የሚቆጣጠሩትን ፕላትሌት የተባሉትን የደም አርጊ ንጥረ ነገሮችን ተሰባስቦ ችግር የመፍጠር ስራ በማዘግየት ነው፡፡ ፕላትሌቶች አደጋ በሚገጥማቸው እና የደም መፍሰስ በሚኖርበት ወቅት፣ እርስ በእርሳቸው በመተሳሰር ግድግዳ ይፈጥሩና የደም መፍሰስን ያቆማሉ፡፡
ነገር ግን ይህ የደም ማርጋት ስራ አንዳንድ ጊዜ ከልክ ያልፍና ወሳኝ የሆኑ የደም ቧንቧዎች ላይ ሲከወን ደም እንደልቡ ወደ ወሳኝ አካላት መድረሱን ያቆማል፡፡ በዚህም ደም ወደ አንጎል መድረስ ያቆማል፣ ስትሮክም ይከሰታል፡፡ በደም ውስጥ ከፍተኛ የቅባት ክምችት መኖር በራሱ የደም ቧንቧዎችን የማጥበብ ሚና ስላለው፣ ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን በደማቸው ያሉ ሰዎች ላይ ከፍቶ ይታያል፡፡
አስፕሪን በሐኪም ትዕዛዝ ስትሮክ ለገጠማቸውና፣ የልብ ድካም ላለባቸው ሰዎች ከመታዘዙ በተጨማሪ፣ በቅርቡ በወጡ ጥናቶች ከካንሰር የመታደግ አቅም ሊኖራቸው እንደሚችልም እየተገለፀ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ባለሞያዎች ግን እነዚህን ተጨማሪ ጥቅሞች እጅግም አይደግፏቸውም፡፡ የእነዚህ ባለሙያዎች ሙግት፣ አስፕሪን አሁንም ብዙ ጥቅሞችን እየሰጠ ያለ በመሆኑና፣ ለብዙ ተጨማሪ ችግሮች የማዘዝ ነገር ሲለመድ ውስብስብ የጎንዮሽ ሂደቶችን ሊያመጣ ስለሚችል ጥንቃቄን ይሻል ባይ ናቸው፡፡
አስፕሪን የእግር እና እጅ መገጣጠሚያዎች ላይ የሚከሰቱ ህመሞችን በመቀነስ በኩልም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡
አስፕሪንን በብልሃት
የአስፕሪንን ለብዙ ወሳኝነት ያላቸው የጤና ችግሮች ጥቅም ላይ መዋል ያዩ ባለሞያዎች፣ የመድሃኒቱን የጎንዮሽ ጉዳቶች ታካሚዎች ብቻ ሳይሆን፣ የህክምና ባለሞያዎችም ጭምር ሊያውቋቸው እንደሚገባ ማሳሰቢያዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ የአስፕሪን ዋነኛ የጎንዮሽ ጉዳት በዋናነት ጨጓራና አንጀት ላይ የሚያደርሱት የመቆጥቆጥና የማድማት አደጋ ነው፡፡ ቀድሞውኑም የጨጓራ ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ጉቱ ይከፋል የሚሉት ባለሞያዎች ተከታዮቹን ዋና ዋና የጥንቃቄ እርምጃዎች ይመክራሉ፡፡
– ማንም ሰው አስፕሪንን ለህመም ማስታገሻነት ከአንድ ቀን በላይ መውሰድ የለበትም፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የአስፕሪን ትዕዛዝ፣ ከሐኪም ሲመጣ ብቻ የሚወሰድ መሆን አለበት፡፡
– የልብ ህመም እና ስትሮክ ተጋላጭ የሆኑና፣ ከዚህ ሰዎችም ቢሆኑ የሚወስዱት የክኒን መጠን በሐኪም ክትትል የሚደረግበት ሊሆን ይገባል፡፡
– አልኮል መጠጦች የአንጀትን የመቆጥቆጥ ተፈጥሮ ስላላቸው፣ ከአስፕሪን ጋር ተደምረው ጉትን ስለሚያከፋ፣ አስፕሪንን በህክምናነት የሚወስዱ ሰዎች አልኮል መጠጦችን ባይዳፈሩ ይመከራል፡፡
– አስፕሪን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መድሃኒት ቢሆንም፣ ያለባለሞያ ትዕዛዝ ከአጭር ጊዜ የህመም ማስታገሻነት ውጪ ያለ አጠቃቀም በሙሉ በባለሞያ ትዕዛዝና ምክር መደረግ አለበት፡፡
The post Sport: አስፕሪን ‹‹ተአምረኛው›› ክኒን appeared first on Zehabesha Amharic.