የደም ግፊት በሽተኛ ነኝ፡፡ በተለያየ ጊዜ ብታከምም ልድን አልቻልኩም፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በሽታው ለተለያዩ ህመሞች ያጋልጣል የሚል ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ ከዚህ መሰል ችግር ራስን ነፃ ለማድረግ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ እንዳለብኝ በዚሁ ህመም የ10 ዓመት ተሞክሮ ያለው አንድ ታካሚ ባልደረባዬ አጫውቶኛል፡፡ ለመሆኑ እንዴት አይነትና በየስንት ጊዜው መመርመር ይኖርብኝ ይሆን? የትስ ቦታ ብመረመር ይሻላል ትላላችሁ? ይኸው አንድ ቀን ያልሆነ ቦታ ሊጥለኝ ይችላል እያልኩ እየሰጋሁ ነው፡፡ በተለይ ትንሽ ድክም ሲለኝ፣ ራሴን ጭው ሲያደርገኝ፣ ድንገት እግሬ ከዳ ሲያደርገኝ ከአሁን አሁን ስትሮክ ሊመታኝ ነው እያልኩ እረበሻለሁ፡፡ ስለዚህ መልሳችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡
መሐመድ ነኝ
ውድ ጠያቂያችን መሐመድ በእውነቱ ከህመሙ በላይ የጎዳህ ጭንቀትህ ይመስለኛል፡፡ ስትሮክ ሳይከሰትብህ በየቀኑ በራስህ ጭንቀት ራስህ ላይ እየጠራኸው ነው፡፡ የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንደሚባለው ጥንቃቄ በሚገባ መተግበር እንጂ ትንሽ እንከን በተሰማህ ቁጥር መበርገጉ ራሱን የቻለ ህመም ነው፡፡ ከደም ግፊት የልቅ የጭንቀት ግፊቱ የበዛብህ ነው የሚመስለው፡፡
ውድ ወንድማችን መሐመድ ከድር መቼም አንድን ህገወጥና ተቀባይነት የሌለውን ድርጊት የፈፀመ ወንጀለኛ መንጥሮ ለማውጣት ፖሊሲው ምርመራ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ ድርጊቱን የፈፀመውም እጁን ካልሰጠ በቀር ታዲያ ፈልጎ ለማግኘት ብዙ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ከቀላል የምስክር ቃል የሚጀምረው ይህ ውስብስብ ምርመራ እስከ ዲኤንኤ ምርመራ ድረስ ይቀጥላል፡፡ ይህ እንግዲህ የፖሊሶችን ጥልቅ ምርመራ ይመለከታል፡፡ ለከፍተኛ ደም ግፊትስ?
ከፍተኛ ደም ግፊትን ያክል በቀላል የማይታይ በደል በአንድ ሰውም ላይ ሲፈፀም ከከባድ ወንጀል ተነጥሎ የማይታይ ነውና ምርመራው እስከ ወዲያኛው ድረስ ሳይቋረጥ ሊቀጥል ይችላል፡፡ የምርመራው አብይ አላማዎችም ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ ህመሙን ያስከተለው ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ/ወንጀል ፈፃሚው መሆኑ ነው/ ሲሆን ሌላው ደግሞ ህመሙ በራሱ ከተከሰተ በኋላ በሌላው የአካል ክፍል ላይ ያደረሰው አደጋ ካለ ለመለየት ነው፡፡ የህመሙ መንስኤ ከተገኘ መንስኤውን በማስወገድ ህመሙን ማስወገድ ወይም ማስተካከል እንዲቻል ያግዛል፡፡ ምርመራው በሌላ የሰውነት ክፍሎች የማስተካከያ እርምጃ/ተግሳፅ/ ለመውሰድ ወሳኝ ይሆናል ማለት ነው፡፡
የምርመራውን ጥቅምና አስፈላጊነት በአጭሩ እንዲህ ከተረዳን ታዲያ እንደ አንተ ያለ ግለሰብ በሐኪም የሚያደርግለት ወይም ሊደረጉለት የሚገቡ ምርመራዎች የትኞቹ ናቸው? ላልከው ጥያቄ እንዲህ አቅርቤያቸዋለሁ፡፡
1. የደም ሴሎች ምርመራ (CBC Count)፡- ይህ ምርመራ የቀይ የደም ሴሎች፣ የነጭ የደም ሴሎችና የፕላትሌቶች ቁጥርን ማወቂያ ሲሆን ጤናማ ቁጥር እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡
2. የሰውነት ማዕድን ምርመራ (Serum Electrolytes)፡- ሰውነታችን ውስጥ በፔሬዲክ ቴብል ውስጥ ካሉት ከ110 በላይ ማዕድኖች (Elements) ውስጥ የማይገኙት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ በዋናነት ግን የደም ውስጥ ሶዲየም፣ ክሎራይድ፣ ፖታሲየም፣ ካልሲየም፣ ፎስፎረስ ጤናማ መጠን እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡
3. የኩላሊትን ጤናማነት መለያ ምርመራ (Renal Function Tests or RFT)፡- ከፍተኛ ደም ግፊትን በማስከተል ረገድ አንዱ ምክንያት ኩላሊት ሊሆን ሲችል ከፍተኛ ደም ግፊትም በራሱ በኩላሊት ላይ ጫና በማድረስ በመጨረሻ ለኩላሊት ድክመት ያጋልጣል፡፡ በመሆኑም የኩላሊትን ጤናማነት ከምንለይባቸው የደም ምርመራ አይነቶች ውስጥ ‹‹ክሬያቲኒን›› እና ‹‹ዩሪያ›› ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንዲሁም የኩላሊትን አካላዊ ጤናማነት ለመመልከት ልዩ የኩላሊት ራጅ ምርመራ (IVP RENAL ANGIOGRAPHY) ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡
4. የደም ስኳር መጠን (Blood glucose test):- ከፍተኛ ደም ግፊትና ስኳር ህመም 50 በመቶ በሆነ ዕድል በጣምራነት የሚከሰቱ ህመሞች ናቸው፡፡ በመሆኑም ለየትኛውም የደም ግፊት ህሙማን የደም ስኳር ጤናማነቱ መታየት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
5. (Urinalysis)፡- ይህ ምርመራ በሽንት ውስጥ የሚኖሩ ኬሚካላዊ ለውጦችን የሚቃኝ ሲሆን በዋናነትም ‹‹albumen›› እና ‹‹glucose›› ለማየት ያግዛል፡፡ በሽንት ምርመራ በተለይ ‹‹albumen›› ከታየ የኩላሊት ህመም መከሰቱን ይጠቁማል፡፡
6. (Lipid Profile):- በምግባችን ይዘት ከፊል ካርቦሃይድሬት፣ ከፊል ፕሮቲንና ከፊል ቅባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ካርቦሃይድሬትና ፕሪቲን ባመዛኙ ወደ ግሉኮስነት /ስኳርነት/ በመቀየር ለሰውነት የኃይል ምንጭ ሲሆኑ የቅባት ምግቦች ደግሞ ወደ ትራይግሊስራይድስ /ቅባትነት/ በመለወጥ ነው ለኃይል ምንጭነት የሚጠቅሙት፡፡ ከፍተኛ የደም ቅባት ክምችት መኖር ለከፍተኛ ደም ግፊትና ስኳር ከማጋለጡም አልፎ ተርፎ የህመሞቹን አደጋም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም የእነዚህን የቅባት ክምችቶች ከምናውቅባቸው የምርመራ አይነቶች ‹‹total cholesterol, low density lipoprotein (LDL), High density lipoprotien (HDL) and Triglycerides›› ተጠቃሽ ናቸው፡፡
7. የታይሮይድ ዕጢ ምርመራ፡- ታይሮይድ ዕጢ የሰውነትን አጠቃላይ አሰራር /ሜታቦሊዝም/ በበላይነት የሚቆጣጠር ሲሆን ከዚህ አብጥ ስራውም ከወትሮ ከፍ ወይም ዝቅ ካለ ለደም ግፊት ህመም ያጋልጣል፡፡ ስለሆነም የዚህን ዕጢ አሰራር የሚጠቁሙ ምርመራዎች እንዳስፈላጊነቱ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ እነሱም (T3/T4 and TSH) በመባል ይታወቃሉ፡፡
8. የልብ ምርመራ፡- ከፍተኛ ደም ግፊት ተፅዕኖ ከሚያሳድርባቸው የሰውነት ክፍሎች ውስጥ ልብ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው፡፡ በመሆኑም የልብን ጤናማነት ከሚያሳውቁ ምርመራዎች ውስጥ ‹‹ኢሲጂና ኢኮካርዲዮግራፊ›› ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በኢኮካርዲዮግራፊ ምርመራ የግራው የልብ ክፍል ላይ ችግር ከታየ ለደም ግፊት ህመሙ ወዲያው መድሃኒት እንዲጀምር ያስገድዳል፡፡
9. የዓይን ምርመራ፡- ይህ ምርመራ ደም ግፊት በዓይን ካሜራ ክፍል ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመለየት የሚያግዝ ሲሆን አስፈላጊ ቅድመ ጥንቃቄያዊ እርምጃ ለመውሰድም ይጠቅማል፡፡
ውድ ወንድማችን መሐመድ ከድር መቼም እንደህመም ተቆጥሮ የማይታከም ነገር ቢኖር ፍቅር ብቻ ነው ይባል እንጂ ከፍተኛ የደም ግፊት ህመም ግን ራሱንየቻለ ህክምና ያለው ነው፡፡ ያውም ከአንድ አይሉ ብዙ አይነት ህክምናዎች አሉት፡፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር አይደል የሚባለው፡፡ ምንም እንኳን መቶ በመቶ ባይፈውሱም፡፡ እናም ታዲያ አማራጩ ብዙ ነው፡፡
እንግዲህ የደም ግፊት ህመም አንድና አንድ የሆነ መድሃኒት የለውም፡፡ የሚዋጡም ሆነ የማይዋጡ መፍትሄዎች ያሉት ነው፡፡ ካለ መድሃኒት አስፈላጊነት የሚታከም የደም ግፊት ህመም አለ፡፡ በአንድ አይነት መድሃኒት ብቻም ይሁን ከአንድ በላይ ጣምራ መድሃኒቶች የማያስፈልጉትም የደም ግፊት ህመም አለ፡፡ ሁሉም እንደየአይነታቸው ህክምናቸው ይለያያል፡፡ የሀገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ እንዲሉ፡፡
መድሃኒት ሁሉ እንደስሙ አይደለም፡፡ የራሱ የሆነ ጉዳትም አለው፡፡ ጉዳቱ ከጥቅሙ ስለሚያንስ ግን እንወስደዋለን፡፡ ከመድሃኒት ሌላ መዳኛ ወይም በሽታውን ማስተካከያ መንገድ ካለ ግን መድሃኒቱን ለመውሰድ በጨረታው አንገደድም፡፡ የግድ መወሰድ ካለበት ወይም አማራጮች ከሌሉ ግን የጎንዮሽ ጉቱን ተቀብለን እንወስደዋለን፡፡ ነገሮች እንዲህ ከመሰሉ ታዲያ የደም ግፊት መጠንህን በአመጋገብ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማስተካከል አንዱ መላ ሲሆን ነገር ግን በመድሃኒት የግድ መታከም አለባቸው የሚባሉ ህመምተኞች የሚከተሉት ናቸው፡፡
የታችኛው የግፊት መጠን ከ90mmhg ቢሆንም የግድ ህክምናው ያስፈልገዋል፡፡
አንድ የደም ግፊት ህመም ታካሚ የግፊት መጠኑ እስከ 140 በ90 mmhg ዝቅ እንዲያደርግ ይመከራል፡፡ ለሁሉም አይነት ህሙማን ግን አይደለም፡፡ አንድ ደባል የስኳር ህመም ያለበት ሰው የደም ግፊት መጠኑ እስከ 130 በ85 mmhg ያህል እንዲወርድ ይመከራል፡፡ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንዳመለከቱትም የትኛው /ዲያስቶሊክ/ የግፊት መጠን ከ90 mmhg እንዳይበልጥ ተደርጎ ቁጥጥር ስር ከዋለ በህመሙ የመሞት ዕድሉ እጅግ አናሳ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተለይ ደግሞ የላይኛውን የግፊት መጠን 120 mmhg ላይ ካደረስከው እጅግ የተዋታለት ቁጥጥር በመባል ይጠራል፡፡
ስለሆነም ወንድማችን ከላይ የተጠቀሱት ምርመራዎች በተለይ ከልብና ከዓይን ምርመራዎች ውጭ በየትኛውም ቦታ የሚታዩ ናቸው፡፡ የምርመራ ጊዜው እንደ ህክምና ታሪክህና ዕድሜህ የሚወሰን በመሆኑ ከሐኪምህ ጋር ቀርበህ ተነጋገርበት፡፡ እነዚህ ምርመራዎች እንዳስፈላጊነቱ ሊደረጉ የሚችሉ እንጂ ለሁሉም የግድ ሊደረጉ የሚገባቸው ናቸው ለማለትም ስላልሆነ የትኞቹ መቼ ሊደረጉ እንደሚገባ ሐኪምህ የበለጠ ግልፅ ሊያደርግልህ ይችላል እላለሁ፡፡ በተረፈ አላህ ከስትሮክ የፀዳ አስተሳሰብ ይስጥህ እያልኩ ልሰናበትህ፡፡