Quantcast
Channel: ጤና – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Health: ወሲብ ብጉርን ካጠፋ ለምን በማስተርቤሽን አይጠፋም? |የዶክተሩን ምላሽ ያንብቡ

$
0
0

እኔ የ22 ዓመትና የአንደኛ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት ስሆን እስካሁን ድረስ የሴት ጓደኛ የለኝም፡፡ ወሲብ የማድረግ ፍላጎ አለኝ፡፡ ግን አላደርግም፡፡ ለምን መሰላችሁ ዘመኑን ፈርቼ ነው፡፡ በተኛሁበትም ዝም ብሎ የዘር ፍሬዬ ይፈሳል፡፡ ምን ይሄ ብቻ እኔም ሴጋ እየተጠቀምኩ በሳምንት ለጌ አፈሳለሁ፡፡ ሴት ልጅ ስመለከት ደግሞ ስሜቴ ወዲያውኑ ይቀሰቀሳል፡፡ ከምንም አይነት ሴት ጋር ልቅ የሆነ ወሲብ አላደርግም፡፡ ፊቴ በጣም ብጉር ይበዛበታል፡፡ ‹‹ይህ ፊትህ ወሲብ ትፈፅም ጥርት ይልልህ ነበር›› ይሉኛል፡፡ እኔ ግን ከማንም ጋር ወሲብ ከማድረግ ሴጋ መጠቀም መርጫለሁ፡፡ ስለዚህ ከእናንተ የምፈልገው ሐኪማዊ ምክርም እውነት ወሲብ ብጉርን ያጠፋል? የብጉር ዋና መንስኤው ምንድነው? ይህ የሴጋ ሥራ በወደፊት ህይወቴ የሚያመጣው ችግር አለ? ውለታ ከፋይ ያድርገኝና የዚህን ጥያቄ መልስ ወደ ኋላ ላታደርጉ ቅድሚያ ሰጥታችሁ እንድታስተናግዱኝ ከወዲሁ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

ከቤ ነኝ

ask your doctor zehabesha

ውድ ከቤ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የአንተ ጥያቄ ቀላል ግምት የምንሰጠው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በበርካታ ታዳጊ ወጣቶቻችን በተደጋጋሚ የሚጠየቅና በህሊናቸውም የሚጉላላ ከመሆኑ አንፃር ደብዳቤህን ስናስተናግደው በታላቅ አክብሮትና ደስታ ነው፡፡

ብጉር በማንኛውም ሰው ላይ በየትኛውም ዕድሜው ሊከሰት የሚችል ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የሚታየው ግን ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳማ ወይም ለአቅመ ሔዋን በደረሱ በአስራዎቹ ውስጥ በሚገኙ ጎረምሶች እና አልፎ አልፎ ደግሞ በሃያዎቹ ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ ነው፡፡

ብጉር እንዲህ ባለ ሁኔታ ከጉርምስና ዕድሜ ጋር በቀጥታ ሊያያዝ የቻለው የራሱ የሆነ ምክንያት አለው፡፡ በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ በሚገኝ ሰው አካል ውስጥ የሚከሰቱ ለየት ያሉ ለውጦች ያሉ ሲሆን በተለይም አካላዊ ለውጦች በጉልህ የሚታዩ ናቸው፡፡ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የሰውነት ቁመት ይረዝማል፡፡ በወንዶች ዘንድ ትከሻ ሰፋ ሰፋ ብሎ የደረትና የእግር እጅ ጡንቻዎች ይፈረጣጥሉ፡፡ ድምፅም እንዲሁ በመጀመሪያ መቆራረጥ፣ ቀጥሎ ደግሞ ይጎረንናል፡፡ ሴቶችም በፋንታቸው ለአቅመ ሄዋ መድረሳቸውን የሚያመላክቱት እንደ ቁመት መጨመር፣ የቆዳ መለስለስ፣ የሰውነት ቅርፅ መዳበርና የጉሮሮ ድምፅ መቅጠን ከዚህ የጉርምስና ለውጥ ውስጥ የሚከተቱ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁሉ ለውጦች የሚመጡት ዕድሜን ተከትለው መሆኑ ታውቋል፡፡ ዕድሜን ተከትሎ የሚመጣው ሌላው ለውጥ ደግሞ ሆርሞን እየተባሉ የሚጠሩ ኬሚካሎች መጠን መጨመር ነው፡፡ በጉርምስና ዕድሜ ወቅት ሆርሞኖች በሰውነታችን ውስጥ ያላቸው መጠን ይለወጣል፡፡ በተለይም የፆታ ሆርሞኖች በደም ውስጥ ያላቸው መጠን ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ በጉርምስና ወቅት ለሚከሰቱ አካላዊ ለውጦች ቀጥተኛ ተጠያቂዎቹም ሌላ ነገር ሳይሆን እነዚህ የፆታ ሆርሞኖች ብቻ ናቸው፡፡

እነዚህ ልዩ የፆታ ሆርሞኖች የጉርምስና ዕድሜን ብቻ ጠብቀው እንዲህ አለቅጥ መብዛታቸው የተፈጥሮን አላማ ለማሳካት በሚል ሲሆን፣ በእዚህ ዕድሜ የሚከሰቱ አካላዊ ለውጦች ወንዱን ለዘር ፈሳሽ አመንጭነት፣ ሴቷን ደግሞ ፅንስን ተሸክማ ለመውለድ መንገድ የሚጠርጉ ናቸው፡፡ ትውልድ ትውልድን እየተካ የሰው ዘር ዝርያውን ከምድረ ገፅ ሳያጠፋ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነቱ የተጣለው በእነዚህ የፆታ ሆርሞኖች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

በጉርምስና ወቅት የወንድና የሴት ልጆች ባህሪም ይቀየራል፡፡ ወንዶች ወደ ሴቶች መመልከትና የሴቶችን ውበት ማድነቅ ይጀምራሉ፡፡ ሴቶችም እንዲሁ፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ አስተሳሰብ ተቃራኒ ፆታዎችን እርስ በእርሳቸው አቀራርቦ ተራክቦ እንዲፈፅሙና ብሎም ዘር እንዲያፈሩ የሚያደርግ ነው፡፡ እንግዲህ ሰዎች ለአካለ መጠን ሲደርሱ አካላዊና ስነልቦናዊ ለውጥ እንዲያመጡና በእነዚህ ለውጦች ተገፋፍተውም ተራክቦ እንዲያደርጉ ያዘዘችው ተፈጥሮ ነች፡፡ ይህን ትልሟን በማስፈፀምም የፆታ ሆርሞኖችን በብዛት እንዲመነጩ ታደርጋለች፡፡

ከእነዚህ የፆታ ሆርሞኖች መካከል በተለይም ቴስቴስትሮን በመባል የሚታወቀው ንጥረ ነገር በቆዳ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ያስከትላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ብጉር ነው፡፡

በጉርምስና ዕድሜ የዚህ ልዩ ሆርሞን መጠን መጨመሩ ስለማይቀር ብጉር መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ሁሉም ሰዎች ይህን የጉርምስና ጊዜ ብጉር ማውጣትን አሳልፈው ነው ወደ ወጣትነት እና ጎልማሳነት የዕድገት ደረጃ የሚዘልቁት፡፡

ሆኖም የአንዳንድ ሰዎች ብጉር ግን ለየት ያለ ነው፡፡ በብዛት አንፃር በጣም ብዙ ነው የሚበቅሉት፡፡ የብጉር እባጮችም ትላልቅና የፊትን ውበት ሊያበላሹ የሚችሉ ናቸው፡፡ ብጉር እንዲህ አለቅጥ እንዲስፋፋ በሚያደርጉት ከሆርሞን በተጨማሪ ማለት ነው ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ታውቋል፡፡

ከእነዚህ መንስኤዎች መካከል አንዱ የህሊና ውጥረት ነው፡፡ ማንኛውም ለውጥ አዲስ ሁኔታን ይዞ ይመጣል፡፡ ያለመዱት ነገር ደግሞ እስኪለማመዱት ድረስ ጭንቀት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ጉርምስናም እንደ ለውጥነቱ ሰዎችን ያስጨንቃል፡፡ ሰውነት በአንዴ ሲመዘዝ፣ ጡንቻ ሲፈረጥም ድምፅ ሲዘበራረቅ እና የፊት ቆዳም በሽፍታዎች ሲዋጥ በእርግጥም ማስበርገጉ አይቀርም፡፡

እንግዲህ በተዘዋዋሪ መንገድ የዚህ ጭንቀት መሰረቱ የፆታ ሆርሞን ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የማህበረሰቡ አመለካከትም ተጨማሪ የጭንቀት መንስኤ ነው፡፡ ማህበረሰቡ በጉርምስና ወቅት ስለሚከሰቱ ለውጦች አስመልክቶ የሚያራምደው እምነት ከእውነታው የራቀ ሲሆን በሚከሰተው የተሳሳተ ግንዛቤ ሳቢያ የሚመጣ ችግርም ነው፡፡

በእርግጥም በጉርምስና ወቅት የሚከሰቱ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ለውጦች ሁሉ አላማቸው የፆታ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሆኖም ይህ ፍላጎት የመነጨው በጎረምሳው ወይም በኮረዳዋ ፍላጎት ሳይሆን በውስጣቸው በሚዘዋወረው ሆርሞን አማካኝነት መሆኑ ግን ግልፅ ሲሆን አይታይም፡፡

በጉርምስና ወቅት ከሚከሰቱት አካላዊ ለውጦች መካከል ወሲባዊ ግንኑነትንም እምብዛም አስተዋፅኦ የሚያበረክተው ብጉር ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከሌሎች ለውጦች ጋር አብሮ ስለተከሰተ ብቻ ብጉር ያለበት ሰው ወሲብ እንደሚያስፈልገው ተደርጎ ሲተረጎም ይታያል፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ትርጓሜ ብቻ ነው፡፡

ብጉርን ያመጣው የፆታ ሆርሞን ነው፡፡ የወሲብ ፍላጎትን ያመጣው የፆታ ሆርሞን ነው፡፡ የፆታ ሆርሞንን ለመቀነስ ቢቻል ብጉር ይጠፋል፣ የወሲብ ፍላጎቱም ይቀንሳል፡፡ ወሲብ ግን ብጉርን ሊቀንስ አይችልም፡፡

ይህን የመሳሰሉ በማህበረሰቡ የሚናፈሱ አመለካከቶች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ላይ ከፍ ያለ ጫና ያመጡባቸዋል፡፡ የብጉር ሽፍታው የጨመረባቸውም ስለወሲብ ስላሰቡ ስለሚመስላቸውና ይህ ያላሰቡት ሐሳብም አደባባይ የወጣ ስለሚመስላቸው ይሸማቀቃሉ፣ ይጨነቃሉ፡፡

ይህ ጭንቀት ግን ቀድሞውንም ከማህበረሰቡ ዘንድ የመጣባቸው እንጂ ወሲብ ባለመፈፀማቸው አለመሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡ ለብጉር ብለው የሚፈፅሙት ወሲብም የማያስፈልግ ከመሆኑም በላይ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ጨምሮ ሌሎች የአባላዘር ህመሞችንና ስላልተፈለገ እርግዝና ያጋልጣቸዋል፡፡

ውድ ኬቢ፡- ብጉር በወሲብ የሚጠፋ ቢሆን ኖሮ አንተ የምታዘወትረው ማስተርቤሽን (ሴጋ) የሚባለው ወሲብ አይነት ድራሹን ባጠፋልህ ነበር፣ ከእንስት ጋር የምታደርገው ግንኙነትም የተለየ ውጤት አያስገኝምና፣ ስለዚህ የሚወራውን ወሬ አትመን፣ በመታቀብህም ፅናበት፡፡

በተረፈ ግን

1. ብጉርን በጣትህ ለማፍረጥ ፍፁም አትሞክር፡፡ ወደ ጠባሳነት ይቀየርብሃል፡፡

2. ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይህ ብጉርህ ይከስምልሃል፡፡

3. አለቅጥ የበዛውን ብጉርህን ሊያስወግዱ የሚችሉ እንደ Doxycycline ያሉ መድሃኒቶች ስላሉ በሐኪም ትዕዛዝና ገዝተህ መጠቀም ትችላለህ፡፡

4. የጉርምስና ለውጥ ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ አንዳንዱ ድምፅ በጣም ይጎረንናል፡፡ አንዳንዱ ቁመቱ በጣም ይረዝማል፣ አንዳንዱ ጡንቻው በጣም ይፈረጥማል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የፊት ላይ ብጉር ይበዛበታል፡፡ ስለዚህም አትጨነቅ እንልሃለን፡፡ መልካም የፊት ውበት!!

The post Health: ወሲብ ብጉርን ካጠፋ ለምን በማስተርቤሽን አይጠፋም? | የዶክተሩን ምላሽ ያንብቡ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>