መንገድ ለማቋረጥ ዜብራው ላይ ስደርስ ረዥም ሊሞዚን ሌሎች መኪናዎችን አስከትሎ ያልፋል፡፡ ወደ ኋላ ከተሰደሩት መኪናዎች የሚሰማውን የሰርግ ዘፈን ብሎም በሚኒባስ ሆነው የሚጨፍሩ አጃቢዎችን እየተመለከትኩ እያለ፣ ከጎኔ ያለው ወጣት ‹‹ነገ ሊፋቱ ዛሬ ይህን ሁሉ ወጭ ማውጣት…›› ሲል ዞር ብዬ አየሁት፡፡
ከቀናት በኋላ ከአራት ኪሎ ወደ ሜክሲኮ የሚሄድ ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬ በሸራተን በኩል ባለው ቁልቁለት መውረድ ስንጀምር፣ ከፊታችን የሰርገኞች መኪኖች በሁለቱም አስፋልት ቆመው ቪዲዮ ይቀርፃሉ፡፡ ፎቶ ይነሳሉ፡፡ ታክሲው ውስጥ ያለን ሰዎች ፀጥ ብለን እስኪጨርሱ ጠበቅን፡፡ ሲጨርሱ አንደኛውን አስፋልት ስለለቀቁልን ሰርገኞቹን አለፍናቸው፡፡ በማለፍ ላይ እያለን ከኋላዬ የተቀመጠ አንድ ግለሰብ ቀደም ብዬ የጠቀስኩትን የወጣቱን አስተያየት የሚመስል አስተያየት አጉረመረመ፡፡ ማግባት እኮ ጥቅም አለው፡፡ ስለጥቅሙስ የተወሰነ ነገር ለምን አልፅፍም ብዙ አሰብኩ፡፡ ስለማግባት የተወሰነ ከፃፍኩ በኋላ ደግሞ መጤን አለባቸው ያልኳቸውን ጉዳዮች አካትቼ የዛሬ ጽሑፌን እንዲህ አሰናዳሁት፡፡
የማግባት ጥቅሞች
በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ መውለድ፣ ማግባትና መሞት የማይቀሩ ወሳኝ ኩነቶች /Standard key events/ ተብለው ቢቆጠሩም ማግባት ግን የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች ማግባትን ከአለማግባት የሚመርጡት በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም የስነ ልቦና፣ የአንትሮፖሎጂ፣ ሶሲዎሎጂና የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች የማግባት ጥቅሞች ናቸው ያሏቸውን በጥናቶቻቸው አሳይተዋል፡፡
የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች እንደሚያብራሩት፣ ማግባት በኑሮ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱብንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለማምለጥ የሚጠቅም ኢንሹራንስ ነው፡፡ ባለትዳሮች አጋሮቻቸው ከሚገልፁላቸው ፍቅር፣ ከሚሰጧቸው እውቅና፣ ለንብረቶቻቸውና ለደህንነታቸው ጥበቃ የተለያዩ ጥቅሞችን የሚያገኙ ሲሆን፣ በዋናነት እነዚህ ተግባራት ውጤታማነታቸውን ያሳድገዋል፡፡ በትዳር አጋሮች መካከል የሚኖረው የኃላፊነት (የሥራ) ክፍፍል ሌላው ኢኮኖሚስቶች የትዳር ጥቅም ብለው የጠቀሱት ጉዳይ ነው፡፡ የባለትዳሮችንና ያላገቡ ሰዎችን የገቢ መጠን ያነፃፀሩ ኢኮኖሚኒስቶች ደግሞ፣ ያገቡቱ ከፍተኛ ገቢ እንዳላቸው ስላገኙ ይህንን ተንተርሰው የገቢ መጨመር ሌላው የማግባት ጥቅም ነው ይላሉ፡፡
የስነ ልቦና፣ አንትሮፖሎጂና ሶሲዎሎጂ ባለሙያዎች ደግሞ ጋብቻ ለማህበረሰብ ወሳኝ ተቋም ነው የሚል የፀና እምነት ያላቸው ሲሆን ማግባት ያለውን ጥቅም በጥናቶቻቸው አስደግፈው ይተነትናሉ፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ (በተለይ ደግሞ ማህበረሰባዊ ባህልን በሚከተሉ ማህበረሰቦች) ያገቡ ሰዎች፣ ካላገቡቱ ይልቅ የኃላፊነት ስሜት አላቸው የሚል እምነት አለ ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡ ይህ ደግሞ ያገቡ ሰዎች ለተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶች ተመራጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ባዮች ናቸው፡፡ ስለሆነም በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ የሚገኘው ደረጃ መጨመር የማግባት ማህበራዊ ጥቅም ነው፡፡
በስነ ልቦና ረገድ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ያገቡ ሰዎች ካላገቡና ብቻቸውን ከሚኖሩ ሰዎች የተሻለ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጤና አላቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ያገቡ ሰዎች ዝቅተኛ የሱሰኝነት ሁናቴና የድብት መጠን ያላቸው ሲሆን ብቻቸውን ከሚኖሩት ይልቅ ረዥም ዕድሜን ይኖራሉ፡፡ ለባለትዳሮች የአጋሮቻቸው መኖር ከውጥረት ማምለጫ (በተለይም ከስራ ይዘውት የመጡትን ውጥረት) ይሆናቸዋል ይላሉ ተመራማሪዎች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አጋር አለኝ (ብቻዬን አይደለሁም) የሚለው ስሜት፣ ባለትዳሮችን ጠንካራ ማንነት እንዲኖራቸውና ዝቅተኛ የብቸኝነት ስሜት ባለቤት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ማግባት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ሁኔታችንን የተሻለ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህም ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ በየቦታው እየተካሄዱ ያሉ ሰርጎች የሚበረታቱና እሰየው የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ማግባትንና መሰረግን፣ የተመለከቱና ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች አሉና መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡
በጋብቻ ዙሪያ መጤን ያለባቸው ሁኔታዎች
1. ያለ ዕድሜ ጋብቻ
በከተሞች የሚደረጉ ጋብቻዎችን በአንክሮ የተመለከተ ሰው፣ በሀገራችን የቤተሰብ ህግ የተቀመጠውን 18 ዓመት የማግቢያ ዕድሜ ያለፉ እንደሆኑ ይታዘብ ይሆናል፡፡ ከዚህም በመነሳት ያለ ዕድሜ ጋብቻ የቀነሰ እንደሆነ ሊያስብ ይችላል፡፡ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጰያ ፊታችንን ስናዞር ግን አሁንም ያለ ዕድሜ ጋብቻ ትልቅ ችግር እንደሆነ ማየት ይችላል፡፡ የተለያዩ ጥናቶችም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ ለአብነት ያህል በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ቀረብህ አስረሴና ሙሉነሽ አበበ፣ በምስራቅ ጎጃምና ደቡብ ወሎ የሚካሄዱ ጋብቻዎችን አጥንተው፣ ውጤታቸውንም እ.ኤ.አ በ2014 በHumanities and social sciense ጆርናል አሳትመውታል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሰረትም በምስራቅ ጎጃም 87 ከመቶ የሚሆኑቱ ተጋቢዎች፣ በደቡብ ወሎ ደግሞ 80 ከመቶ የሚሆኑቱ ተጋቢዎች ከ18 ዓመት በታች ዕድሜያቸው አግብተዋል፡፡ ሌላው በዚሁ ጥናት የተገኘው ውጤት ያለ ዕድሜያቸው ካገቡት ሰዎች ውስጥ 83 ከመቶ የሚሆኑቱ ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 17 ከመቶ የሚሆኑቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡ ይህ ውጤት የሚያሳየን አሁንም ያለ ዕድሜ ጋብቻ ችግራችን መሆኑንና ወንዶችም የችግሩ ገፈት ቀማሾች እንደሆኑ ነው፡፡
2. የተጋቢዎች የደስታ መጠን መቀነስ
ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ማግባት የተለያዩ ጥቅሞች አሉት፡፡ ይህ ሁኔታም ያገቡ ሰዎችን ካላገቡቱ በተሻለ መልኩ ደስተኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል ይላሉ ስቱትዘርና ፍሬይ የተባሉ ባለሙያዎች በ2006 ባሳተሙት ጽሑፍ፡፡ እንደ ሙያተኞቹ ማህበራሪያ በጭራሽ ያላገቡቱ የደስታ መጠናቸው ከቀድሞው ዘመን በተሻለ እየጨመረ፣ በተቃራኒው ያላገቡቱ የደስታ መጠናቸው ከቀድሞው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎች በጀርመን በሚገኙ 15,268 ሰዎች ላይ ከ1984 እስከ 2000 ባደረጉት የ17 ዓመት ጥናት፣ ተጋቢዎች በተጋቡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከፍተኛ የደስተኝነት መጠን እንዳላቸው ያም በሂደት እየቀነሰ እንደሚመጣ አይተዋል፡፡
3. የፍቺ መጠን መጨመር
ከተጋቢዎች የደስታ መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ ሌላው ጉዳይ የፍቺ መጠን መጨመር ነው፡፡ ይህ ክስተት ዓለም አቀፋዊ ሲሆን በምዕራቡ ዓለም መጠኑ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአሜሪካና በካናዳ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሁለት ትዳሮች አንዱ በፍቺ ይቋጫሉ፡፡ ግሎባላይዜሽን እና የግለሰባዊነት ባህል መስፋፋት ይህንን የፍቺ መጠን በምስራቁ ዓለምም እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ በእኛም ሀገር ይህ ክስተት መጨመሩን የሚያሳዩ ጠቋሚዎች አሉ፡፡ ለአብነት በማዕከላዊ ስታስታስቲክስ ኤጀንሲ የቀረቡ መረጃዎችን በመተንተን ላቅርብ፡፡
በኤጀንሲው ሀገር አቀፍ ጥናት እንደሚታየው፣ ከ15 እስከ 49 ዓመት ከሚገኙ ሴቶች ውስጥ 61.4 ከመቶ የሆኑቱ ያገቡ ሲሆን 7.7 ከመቶ የሚሆኑቱ ደግሞ የተፋቱ ናቸው፡፡ ኤጀንሲው እ.ኤ.አ በ2011 ወንዶችንም ሴቶችንም ያካተተ ተመሳሳይ ጥናት አካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ በንፅፅር ያህል ሴቶቹን የተመለከተውን መረጃ እንመልከት፡፡ በ2011 ወንዶችንም ሴቶችንም ያካተተ ተመሳሳይ ጥናት አካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ ለንፅፅር ያህል ሴቶቹን የተመለከተውን መረጃ እንመልከት፡፡ በ2011 በተደረገው ጥናት 58.1 ከመቶ የሚሆኑቱ ያገቡ ሲሆን 5.3 ከመቶ የተፋቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ጥናቶች የሚያሳዩን በ3 ዓመት ውስጥ ያገቡ ሴቶች መጠን ከ58.1 ወደ 61.4 ያደገ ሲሆን፣ የተፋቺዎቹ መጠን በወገኑ ከ5.3 ወደ 7.7 ከመቶ ጨምሯል ማለት ነው፡፡
4. የጋብቻ ወጭ መጨመር
ያለ ዕድሜ ጋብቻ ላይ ምርምሮችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራው ፖፑሌሽን ካውንስል የተባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በ2011 ባሳተመው አጭር የምርምር መገለጫ፣ በታዳጊ ሀገራት ለጋብቻ የሚወጣው ወጭ በጣም ጨምሯል፡፡ ይህም ተጋቢዎቹ በዓመት ከሚያገኙት ገቢ በላይ ሆኗል፡፡ ይህንን የጋብቻ ወጭ መጨመር ኢትዮጵያዊ ጥናቶችም አረጋግጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 አየለ ተሰማ የተባለ ተመራማሪ ለሶስተኛ ዲግሪ በሰራው ጥናት፣ በወላይታ ዞን ገጠራማ ቦታዎች ስሚከናወኑ የሰርግና የለቅሶ ወጪዎች የሰጠው ትንተና ለዚህ እባባሌ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡
አየለ እንዳረጋገጠው ለሰርግና ለለቅሶ የሚወጣው ወጭ ከፍተኛ ሲሆን የሰርግ ወጭው ለለቅሶ ከሚወጣው ወጭ ይበልጣል፡፡ የሰርግ ወጪውን ሲተነትን የሙሽራውና የሙሽሪት ቤተሰቦች ያጠራቀሙትን የምግብ ክምችት/ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ የቤት እንስሳትን ይሸጣሉ ወይንም ያርዳሉ፡፡ ገንዘብ ያበድራሉ፡፡ የእርሻ መሬታቸውን ያከራያሉ፡፡ብሎም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ታዳሚዎች ይጠራሉ፡፡ በምላሹ ታዳሚዎች ስጦታዎችን የሚሰጡ ሲሆን እነዚህ ስጦታዎች ግን ለሰርግ የሚወጣውን ወጭ 20 ከመቶ የሚሆነውን ብቻ ይሸፍናሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አየለ እንደሚያብራራው፣ ከጋብቻው በኋላ የተጋቢ ቤተሰቦች የተለያዩ ነገሮችን (ለምሳሌ ቤት፣ የቤት ዕቃ፣ በሬና ትንሽ መሬት) መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአጠቃላይም ይላል የአየለ ጽሑፍ ለጋብቻ የሚመጣው ወጭ ከቤተሰቦቹ ዓመታዊ ገቢ ይበልጣል፡፡ ማህበራዊ ግንኙነትን ማጠናከር፣ የቤተሰቡን ክብር መጠበቅ/ማጎልበት፣ ከህብረተሰቡ የሚመጡ ጫናዎች፣ ከሌሎች ጋር የሚደረጉ የድግስ ውድድሮችና ከፍተኛ ስጦታ አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ፣ ለሰርጎች ትልቅ ወጭ እንዲወጣ የሚያደርጉ ምክንያቶች ሆነው በአየለ ጥናት ተረጋግጠዋል፡፡
ሠርግ በዋናነት የሚከናወነው፣ የተጋቢዎችን ትዳር መመስረት ማህበራዊና ህጋዊ ዕውቅና ያገኝ ዘንድ ነው፡፡ ይህን ለመከወን የሚወጣው ወጭ ሲበዛ፣ በተጋቢዎችም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ የራሱ የሆኑ ተፅዕኖዎችን እንደሚፈጥር ይታወቃል፡፡ በማህበረሰብ ደረጃ ደግሞ የሰርግ ወጪዎች መጨመር ሁለት አብይት ተፅዕኖዎች አሉት፡፡ የፓፑሌሽን ካውንስል የ2011 ጥናት እንደሚያሳየው፣ የሙሽሪት ቤተሰቦች የሚያወጡት ወጭ ከፍተኛ በሆነበት ማህበረሰብ (ለምሳሌ ለሙሽራው ቤተሰቦች ስጦታ የሚሰጥበት ባህል) የሰርግ ወጪዎች መጨመር ያላገቡ ሴቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በተቃራኒው የሙሽራው ቤተሰቦች የሚያወጡት ወጭ ከፍተኛ የሆነበት ማህበረሰብ ወጣቶችን ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነቶችን እንዲፈጥሩና ልጆች እንዲወልዱ አድርጓቸዋል፡፡ በአጠቃላይም የጋብቻ ወጪዎች መጨመር፣ ወጣቶችን ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነቶችን እንዲፈጥሩና ያላገቡ ሴቶች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
ለዚህ ወጭ መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀመጡም፣ በቁሳዊ ነገሮች ዋጋ የመስጠት ሁናቴ ዋነኛ መንስኤ ነው ባዮች ናቸው ስቱትዘር እና ፍሬይ የተባሉ ባለሙያዎች፡፡ ለዚህም አብነት ሲያቀርቡ በተለያዩ መጽሔቶችና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውድ የሆኑ የሰርግ ድግሶች ሽፋን ያገኛሉ፡፡ ይህም ሰዎችን ወደ ከፍተኛ ወጭ የሚያስወጡ ድግሶች እንዲያመሩ ያደርጋ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ከፍተኛ ወጭ አውጥተው ትዳር የመሰረቱ ሙሽሮች፣ ቆይታቸው አጭር ብሎም ትንሽ አዎንታዊና ብዙ አሉታዊ ግንኙነቶች እንደሚታይባቸው የተለያዩ ቀደምት ጥናቶችን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
5. ትዳርን/ፍቅርን ዘላቂ ለማድረግ ዝግጁነት አለመኖር
ፍቅርን ብሎም ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ፣ ሶስቱም የፍቅር መዋቅሮች (መቀራረብ፣ ስሜታዊ መፈላለግና ዝግጁነት/መስዋዕትነት) መኖር አለባቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ የስሜት ፍቅር መገለጫቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህ አባባሌ የጅማ ዩኒቨርሲቲው ፈንቴ አምባለው በ2009 የሰራውን ጥናት እንደ ማስረጃ ላቅርብ፡፡ ፈንቴ ጥናቱን የሰራው 828 በሆኑ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ሲሀን፣ በጥናቱ መሰረትም ተማሪዎቹ ከፍተኛ የሆነ የስሜታዊ ፍቅር መጠን ታይቶባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ ደግሞ የፍቅር ፊልሞችን በተደጋጋሚ የሚያዩ፣ ከፍቅር ጋር የተያያዙ ጽሑፎችን የሚያነቡ ወይም ከፍቅር ጋር የተያያዙ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን የሚያደምጡ ተማሪዎች ከሌሎች የበለጠ የስሜታዊ ፍቅር መጠን አሳይተዋል፡፡ በመሰረቱ የስሜት ፍቅር መቀራረብና መፈላለግ ያለበት ፍቅር ሲሆን፣ ፍቅርን ለማስቀጠል የሚያስችለውን ዝግጁነት ያልያዘ የፍቅር አይነት ነው፡፡ ይህንን ፍቅር መሰረት አድርገው ወደ ሰርግ የሚዘልቁ ሙሽሮች መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን መገመቱ ደግሞ ቀላል ነው፡፡
6. ግጭቶችን የመፍታት ችሎታ ያላዳበሩ ሙሽሮች
በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ውስጥ ሁሌም ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች በግንኙነቶች መሀል ግጭቶች ከሌሉ መጀመሪያውኑ ግንኙነቱ የለም ማለት ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ውስጥ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ጊዜም ግጭቶችን የመፍታት ችሎታ ወሳኝ ነው፡፡
መጋባት አንዱ የሁለትዮሽ ግንኙነት አይነት ነውና ይህ ግጭቶችን የምታት ችሎታ ማዳበርን ይጠይቃ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን አይነት ችሎታን አዳብረው ወደ ትዳር የሚዘልቁ ኢትዮጵያውያን ሙሽሮች ስንት ይሆኑ ብለን ስንጠይቅጥቂት ይሆናል መልሱ፡፡ ማስረጃ ለማቅረብ ያህል፣ አስካለማርያምና ምን ዋጋው የተባሉ ተመራማሪዎች በአምስት ወረዳዎች የሚታዩ ፍቺዎችን መርምረው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ2001 እስከ 2003 ለተፈፀሙ ፍቺዎች ሶት አበይት ምክንያቶችን ሲኖሩ ግጭቶችን የመፍታት ችሎታ አለመኖር አንዱ ነው፡፡
7. የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት
የትዳር አጋር ከመምረጥ ጀምሮ በሌሎች ጉዳዮችም ጭምር፣ የተጋቢ ቤተሰቦች ጣልቃ ገብነት እንደሚታይ የፋፍቻምፕስ እና ኩስምቢንግ የ2002 ጥናት አሳይቷል፡፡ የጣልቃ ገብነቱን ችግር ሲያብራሩ ወላጆች በአጋር መረጣ ላይ ትከረታቸውን ሀብት ላይ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ልጆች ደግሞ የሙያ ወይም የግለሰባዊ ፍላጎቶች መመሳሰል ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ከአጋር መረጣ በኋላም ቢሆን፣ የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት እንዲቀጥል እናም በተጋቢዎቹ ላይ ችግር እንደሚፈጥር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እላይ የጠቀስኩት የእነ አስካለማርያም ጥናት፣ የፍቺ መንስኤ ብሎ ነቅሶ ካወጣቸው አበይት ምክንያቶች ሁለተኛው የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ነው (የመነጋገር ችግር ሶስተኛው መንስኤ ነው)፡፡
The post Health: ከሰርግዎ በፊትና በኋላ ሊያጠኗቸው የሚገቡ 7 ወሳኝ ጉዳዮች appeared first on Zehabesha Amharic.