Quantcast
Channel: ጤና – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Health: ለቤተሰቦቻቸው፣ለአገራቸውና ለዓለም መመኪያ የሚሆኑ ልጆችን ማፍራት የሚቻለው በአጋጣሚ ወይስ በዕድል?

$
0
0

ask your doctor zehabesha

ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁል ጊዜ የልጆቼ ጉዳይ የሚያሳስበኝ ተምረው ለአገር የሚጠቅሙ እንዲሆኑ በበኩሌ ማድረግ ያለብኝን ሳላደርግ እንዳልቀር ነው፡፡ እናም በዚህ ረገድ ዘሃበሻ መልስ የሚሆን መልዕክት አታጣም ብዬ ይህችን አጭር ጥያቄ ላኩላችሁ፡፡ መልሳችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡

የእናንተው አንባቢ የውብ ዳር

የእኛ ምላሽ!

‹‹ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች›› ብሎም ሀገር ተረካቢዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ በአስተዳደጋቸው አስፈላጊው ሁሉ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ያስፈልጋል፡፡

ሲግመንድ ፍሮይድ የተባለው የማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ተመራማሪ፣ (ኢፌክትስ ኦፍ ፓረንቲንግ ኦን ቻይልድ ዴቨሎፕመንት) በሚለው ጥናቱ አንድ ህፃን ተወልዶ 7 ዓመት እስኪሞላው ድረስ፣ የሚደረግለት አካላዊና ሞራላዊ ድጋፍ የልጁን የወደፊት ማንነት እንደሚወስን ይናገራል፡፡

በዚሁ ጥናት ሌሎች ተመራማሪዎች፣ በልጆች ሁለንተናዊ ሰብዕና ላይ ያነሷቸው የክርክር ነጥቦችም ተካተዋል፡፡ የተከራካሪው አንደኛ ወገን ‹‹ልጆች ሲወለዱ እንደ ባዶ ወረቀት ናቸው፣ ምንም አይነት ባህሪም ሆነ ዕውቀት ይዘው አይመጡም፣ ሰብዕናቸው የሚቀረፀው ወደዚህች ምድር ከመጡ ጀምሮና በምናሳያቸው እንክባቤና ምልክት ነው›› ሲል ሌላኛው የክርክር ቡድን ደግሞ ‹‹የለም! የአንድ ህፃን ባህሪ የሚወሰነው በዘር ነው፣ ሲለድ ጀምሮ የአባት የእናቱ ወይም ከዚያ ቀደም ያሉትን አያቶቹን ባህሪና ዕውቀት ይጋራል፡፡ ከተወለደ በኋላ የምናደርግለት እንክብካና ከማህበረሰቡ የሚያገኘው ምላሽ፣ በልጁ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ያስከትላል›› ይላል፡፡ ለዚህ ጥናቱ እንደ ማጠናከሪያነት የሚጠቀመው ሐሳብ፣ የልጆች ባህሪ አለመመሳሰል፣ የአንድነትና የስኬት መለያየትን ነው፡፡

እነዚህ ሐሳቦች ለበርካታ ዓመታት ሲያከራክሩ ቆይተው፣ በስተመጨረሻ ተቀባይነት ያገኘው፣ የሰው ሰብዕና የሚወሰነው በእርግጥ ከቤተሰብ የምጋራቸው ነገሮች እንደተጠቀቡ ሆነው በአስተዳደግ ሂደት ውስጥ ከቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤትና ማህበረሰብ በምንቀስማቸው ዕውቀቶችና ባህሪዎች ይሆናል፡፡

አንዳንድ ወላጆች ስለልጆች አስተዳደግ ያላቸው አመለካከት የተገደበ ነው፡፡ ልጆች መሰረታዊ ፍላጎታቸው ከተሟላላቸው ከቤተሰብ መጠበቅ እንደሌለባቸው ያምናሉ፡፡ ሌሎች ወላጆች ደግሞ ለልጆቻቸው ከመሰረታዊ ፍላጎታቸው በተጨማሪ፣ መጫዎቻዎችን መግዛትና የተለያዩ ስፍራዎች መውሰዳቸውን የእንክብካቤ መጨረሻ አድርገው ይወስዱታል፡፡ እርግጥ ነው ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ድርጊቶች፣ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው አቅም በፈቀደ መልኩ ሊፅሙት የሚገባ መልካም ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን ልጆች ከምንም በላይ የስሜት ድጋፍ ማግኘትን ይፈልጋሉ፡፡

እንግዲህ የስሜት ድጋፍ በተለያየ መልኩ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ልጆች ሲናገሩ ማድመጥ፣ አዳዲስ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አድናቆት መለገስ፣ ራሳቸውን እንዲሆኑና በራሳቸው እንዲተማመኑ ማበረታታት፣ የበታችነት እንዳይሰማቸው ማገዝ የመሳሰሉት የስሜት ድጋፎች ለአንድ ህፃን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በባለትዳሮች መሀል ልጅ ሲፈጠር ትዳር ይባረካል፣ የወላጆችም ደስታ ወደር አይኖረውም፣ ይሄንንም ደስታ አስጠብቆ ለማቆየት ወላጆች አቅማቸውና ዕውቀታቸው በፈቀደ መጠን ልጆቻቸውን የተሻለ ዜጋ አድርገው በማሳደግ ጥረት ሲያደርጉ እናስተውላለን፡፡ በመሆኑም ወላጆች ቀዳሚ የልጅነት ጊዜ ላይ የሚያከናውኗቸው ድርጊቶች፣ በልጆቻቸው የወደፊት ህይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ልጆችን በማሳደግ ሂደት ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

(Baum rind D) የተባለች የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ፣ በተለያዩ ወላጆችና ስለሚተገበሩ የልጆች የአስተዳደግ አይነቶችና ውጤቶቻቸው በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ወላጆች ላይ ጥናት አካሂዳለች፡፡ አምስት ዓመት በፈጀው በዚህ ጥናቷም ለማህበረሰቡ ይጠቅማሉ ያለቻቸውን አራት የልጆች አስተዳደግ አይነቶችን አሳውቃለች፡፡ እነዚህም ‹ፈላጭ ቆራጭ›፣ ‹ሚዛናዊ›፣ ‹ነፃ› እና ‹ቸልተኛ› በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

1. ፈላጭ ቆራጭ፡ ይሄ አይነት አስተዳደግ ወላጆች ህግና ደንብ በማውጣት፣ ልጆች ምንም አይነት ጥያቄ ሳያቀርቡ የወጣውን ህግና ደንብ እንዲያከብሩ ያስገድዳል፡፡ ልጆች እቤት ውስጥ ባለው የዕለት ተዕለት ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ አይኖራቸውም፡፡ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች፣ በተጣለባቸው ሕግና ገደብ ‹ለምን?› ብለው ቢጠይቁም፣ የሚሰጣቸው ምላሽ ‹‹እኔ ስላልኩ ይህን ማድረግ ይኖርብሃል›› የሚል ይሆናል፡፡ ሕግና ደንቡን ሲጥሱም የተደነገገ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡

በፈላጭ ቆራጭ ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች በአብዛኛው

– ህግና ደንብ በማክበር ይታወቃሉ፡፡

– እልኸኛ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

– ዝቅተኛ የሆነ በስራ መተማመን ይስተዋልባቸዋል፡፡

– ከሰው ጋር ያላቸው ተግባቦት በጣም ዝቅተኛ ይሆናል፡፡

– በትምህርት ቤት ቆይታቸው መልካም የሚባል ባህሪ ይስተዋልባቸዋል፡፡

2. ሚዛናዊ፡

ሚዛናዊ የሆነ የአስተዳደግ ዘዴ የሚከተሉ ቤተሰቦች፣ እንደ ፈላጭ ቆጮቹ ሁሉ የቤተሰብ ህግና ደንብ ያወጣሉ፡፡ ሆኖም የእነዚህን የሚለየው የሚያወጡትን ህግና ደንብ አላማውን ያስረዳሉ፡፡ አንዳንዶቹም የቤተሰቡን ሕግ ከልጆቻቸው ጋር በትብብር ያወጣሉ፡፡ ሕጉ ሲጣስም ምን መቀጣት እንዳለባቸው የመወሰን እድሉንም ይሰጧቸዋል፡፡ ልጆቹም የቤቱን ህግና ደንብ ሲጥሱ የሚጠብቃቸው ቅጣት ራሳቸውን ዝግጁ ስለሚያደርግ፣ በውስጣቸው ጥላቻን ሲያሳድሩ አይስተዋሉም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስነ ምግባራቸውን ለማበረታታት ወላጆች የተለያዩ ስጦታዎችን ያበረክቱላቸዋል፡፡ ሚዛናዊ አስተዳደግን በሚጠቀም ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ በአብዛኛው፡፡

– ደስተኛ እና ስኬታማ ይሆናሉ፡፡

– ከፍተኛ የሆነ የውሳኔ ብቃት ሲታይባቸው፣ በውሳኔ ጊዜም የተለያዩ አማራጮችን መመልከትና ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችንም ቀድመው ለመገመት ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡

– በህይወታቸው ላይ ኃላፊነትን የሚስዱ ግለሰቦች ይሆናሉ፡፡

– ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን ይታይባቸዋል፡፡

– ራሳቸውን መግለፅ ይችላሉ፡፡

– የሰውን ሐሳብ የመቀበል ችግር አይኖባቸውም፡፡

– በአጠቃላይ ለህይወት በጎ የሆነ ዕይታ ያዳብራሉ፡፡

– በቀላሉ ራሳቸውን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ማለማመድ ይችላሉ፡፡

3. ነፃ አስተዳደግ

ይህን የአስተዳደግ ዘዴ የሚጠቀሙ ቤተሰቦች፣ ምንም አይነት ህግ እና ደንብ ለቤታቸው አያወጡም፡፡ ለልጆቻቸው ያስፈልጋሉ ያሉትን ቁሳቁስ በራሳቸው ተነሳሽነትም ሆነ በልጆቹ ጠያቂነት ከማሟላት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ‹‹ልጆች ልጆች›› ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ጥፋታቸውም ከልጅነታቸው ጋር የተያያዘ እንጂ በወደፊት ህይወታቸው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን የባህሪ ብልሹነት አይቀበሉትም፣ ሁሉንም ነገር ሲያድጉ ይተዉታል ብለውም ያስባሉ፡፡ ከልጆቻቸው ጋር ሊወያዩ የሚችሉት ምናልባት እቤት ውስጥ ከባድ የሚባል ችግር ሲፈጠር ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ቢሆን የተፈጠረውን ችግር ወይም ልጁ የሚያንፀባርቀውን መልካም ያልሆነ ባህሪ ለማስተካከል ብዙም ጥረት አያደርጉም፡፡ ከልጆቸው ጋር የሚኖራቸውም ግንኙነት የወላጅ እና የልጅ ሳይሀን የጓደኛ አይነት ነው፡፡

ነፃ አስተዳደግን በሚጠቀም ቤተሰብ ውስጥ የሚያድግ ልጅ የሚያንፀባርቃቸው ባህሪዎች በአብዛኛው፡-

– ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን ይስተዋልባቸዋል፡፡

– በሚፈልጉት ጊዜ ማንኛውንም ነገር እንደሚያገኙ ያምናሉ፡፡

– ሕግና ደንብን ያለማክበር ችግር ይታይባቸዋል፡፡

ወላጆቻቸው ሁሉንም ነገር እየሰጡ ስላሳደጓቸው፣ በትምህርት ህይወታቸውም ሆነ ስራ ላይ፣ ይሄነው የሚባል ጥረት ስለማያሳዩ እኔ ብቻ የተሻልኩ ነኝ ብለው ስለሚያስቡ ስኬት ሲርቃቸው ይስተዋላል፡፡ ዝቅተኛ የሆነ የድብርት መጠን ይስተዋልባቸዋል፡፡

4. ቸልተኛ

እነዚህ አይነት ቤተሰቦች በአብዛኛው፣ የልጆቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎት እንኳን በአግባቡ የማያሟሉ ናቸው፡፡ የእነሱ እምነት ልጅ በዕድሉ ያድጋል የሚል ሲሆን በራሳቸው ተፍጨርጭረው ህይወታቸውን እንዲለውጡ ይጠብቃሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ልጆች በስራና በሌላው ህይወታቸው በጣም የተዋጡ ወይም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሱስ ተጠቂዎች፣ የአዕምሮ በሽተኞች ወይም ደግሞ በልጅነት ዘመናቸው ከቤተሰባቸው ወይም ከማህበረሰቡ መልካም እንክብካ ያልተደረገባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶቹ ያመለክታሉ፡፡ እንደ ጥናቱ ምናልባት ልጆቹ የተፈጠሩት ሁለቱም ወላጆች፣ ልጅ ወልደው ለማሳደግ ዝግጁ ሳይሆኑ ወይም በአንደኛው ወገን ግፊትና ፍላጎትም ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል፡፡

እንደዚህ አይነት ባህሪ በሚንፀባረቅበት ቤተሰብ ያደጉ ልጆች በአብዛኛው

– ለመኖር አስፈላጊ የሆነ የህይወት ልምድና ክህሎት ማጣት ይስተዋልባቸዋል፡፡

– በሱስ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

– የወላጆቻቸውን በቂ ፍቅርና አትኩሮ ሳያገኙ ያደጉ ስለሆነ፣ ካደጉ በኋላም የሰውን ‹አትኩሮት የመሳብ ይስተዋልባቸዋል፡፡

– ዕድሜያቸው ለተቃራኒ ፆታ ፍቅር ሲደርስም፣ ተፈላጊነታቸውን ለማረጋገጥ ከቀረቧቸው ሰዎች ጋር ሁሉ በቀላሉ በፍቅር የመውደቅ አባዜ ይስተዋልባቸዋል፡፡

– በአብዛኛው ወንጀል በመፈፀም የሚታወቁ ግለሰቦች ከዚህ አይነት ቤተሰብ እንደመጡ ይኸው ጥናት ያመለክታል፡፡

ምን ይደረግ?

ከላይ በመግቢያችን የጠቀስናት ተመራማሪ በጥናቷ ያሰፈረችው፣ ልጆችን በማሳደግ አስፈላጊ የሆነው ነጥብ (Responsiveness and demanding) ኃላፊነትን መወጣትና ከልጆች መጠበቅ የሚል ሲሆን፣ ከዚህ እሴት አኳያ እያንዳንዱን የአስተዳደግ ዘዴ እናያለን፡፡ ፈላጭ ቆጭ የልጅ አስተዳደግ ዘዴ (Demanding not responsive) ተብሎ የሚፈረጅ ሲሆን፣ እንዲከበርለት የሚፈልጋቸውን የቤተሰብ እሴቶች ከመዘርዘር ውጪ ልጁ ከቤተሰቡ የሚፈልጋቸውን ቅድመ ሁኔታ ስለማያሟላ፣ ተመራጭ ያልሆነ የልጅ አስተዳደግ መሆኑን ትገልፃለች፡፡

ነፃ የሆነ የቤተሰብ አስተዳደግን ስንመለከት ደግሞ (Responsive but not demanding) ይህም ማለት፣ ቤተሰቡ ለልጁ የማያቋርጥ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ፣ ሆኖም አንድ መልካም እሴት ወይም ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጥ በመሆኑ፣ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ትላለች፡፡

ቸልተኛ የሚባለው አይነት ባህሪ የሚንፀባረቅባቸው ወላጆች፣ ለህይወት አስፈላጊ የሆኑት (Neither Responsiveness Not demanding) ተብሎ የሚፈረጅ የአስተዳደግ አይነት ስለሆነ እጅግ አደገኛ የአስተዳደግ አይነት መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

በመጨረሻም የጥናቱ ማጠቃለያ እንዳሰፈረው፣ Demanding (ሚዛናዊ) የሚባለው የአስተዳደግ አይነት ‹‹Bothe responsive and emanding›› በመሆኑ፣ እጅግ ተመራጭና ለልጁ ሁለንተናዊ ዕድገት አዎንታዊ የሆነ ተፅዕኖ የሚያሳድር፣ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ወላጆች ቢከተሉት መልካም ውጤት እንደሚያመጣ ይታመናል፡፡ እንግዲህ የዛሬው ህፃን፣ የነገው አባወራና ሐገር ተረካቢ ነውና በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ ልጆቻችንን በማሳደግ ሂደት ውስጥ ለምናከናውናቸው ተግባሮች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልጆች የምንፈልገውን ነገር እንዲያደርጉ ከመናገር ይልቅ፣ ምሳሌ ሆኖ መገኘቱ ከሁሉም በላይ ተመራጭ ስለሆነ፣ የመልካም ባህሪ ባለቤትነት ፈርቀዳጅ በመሆን የመልካም ቤተሰብ ባለቤት መሆን ይችላል እላለሁ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>