ከቅድስት አባተ | ዘ-ሐበሻ
በጠዋት መነሳት ለእርስዎ ምን ስሜት ይፈጥርቦት ይሆን? ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የሰው ዘር በጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ የመደበትና የመጫጫን ስሜቶችን ያስተናግዳል፡፡ አንዳንዶቹም ከሀይለኛ የእንቅልፍ ስሜት ለመውጣት ሲቸግራቸው የስራ መስካቸውን እስከ መቀየር ይገደዳሉ፡፡ በንቁነት ጊዜያዊ ፈውስን ይሰጣሉ ተብለው የሚታመንባቸው እፆችንና መጠጦችን መጠቀምም የብዙዎች የዓለማችን ህዝቦች ልማድ እየሆነ መጥቷል፡፡ የቡናና ሻይ መወዳጀትም ለንቃት እንደመፍትሄ ሲቆጠር የነበረ፣ ዛሬም የሚኖር ልማድ ሆኗል፡፡ ምስጋና ለጥናትና ምርምር ይግባውና የሚከተሉት ነገሮች ከቡና ባልተናነሰ መልኩ ለንቃት መፍትሄ እንደሚሆኑ ተረጋግጧል፡፡
1. ፖም
ይህ መልከመልካም የአትክልት አይነት ከምግብነት በተሻለ መልኩ ለብዙ ህመምና ችግሮች በመፍትሄነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ፖም በውስጡ ፍሩክቶስ የተሰኘ ንጥረ ነገር ይዟል፡፡ ይህ ንጥረ ነገርም በተፈጥሮ የስኳርነት ባህሪ ያለው በመሆኑ
አዕምሯችን በተፈጥሮው የነቃ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ፍሩክቶስ በሰውነታችን ውስጥ ያለምንም መረበሽ በዝግታ በመጓዝ በደረሰባቸው የትኞቹም የአካል ክፍላችን ውስጥ የሚገኙ የደምስሮቻችንና ጡንቻዎቻችንን የማነቃቃት ባህሪ አለው፡፡
2. ጨው ማሽተት
ለወትሮው ከምግባችን ውስጥ የማናጣው የምግብ ጨው ጠቀሜታውን በማስፋት ሊያነቃቃን መጥቶል ሲል ምንኛ ይገርመን ይሆን? መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ፖሊሶች ከእንቅልፍ በሰዓቱ ለመንቃት ሲሉ ጨውን ተመራጭ ያደርጋሉ፡፡ እንደዘገባው ከሆነ ጨውን በአፍንጫ ማሽተት በድብርት ውስጥ ያለ አዕምሮን በፍጥነት በማንቃት ከእንቅልፍ ስካር ውስጥ መንጥቆ ያወጣናል፡፡ ሆኖም ምንም እንኳን ጨውን በቀላሉ ማግኘትና መጠቀም የሚቻል ቢሆንም በምናሸትበት ወቅት ለሳይነስ በሽታ እና ለአዕምሮ ጉዳት ሊዳርግ የሚችል አቅም ያለው በመሆኑ በተደጋጋሚ ለንቁነት ተብሎ መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱን ያመዘነ ያደርገዋል፡፡
3. ሙዝ
ይህ የፍራፍሬ አይነት በዘርፈ ብዙ ጥቅምን የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመጠጥ ሀንጎቨር የተደበተ ሰውነትን ለማነቃቃት ከምግብ በፊት ሙዝ መብላት ፍቱን መፍትሄ ነው፡፡ የምግብ ፍላጎትን ማጣትና ማቅለሽለሽ ስሜት የሚሰማው በሽተኛው ሙዝን ቢመገብ ራሱን
ለማረጋጋት የሚጠቅመው ይሆናል፡፡ በተለይም ይህ የፍራፍሬ ዝርያ በብዛት በወሰዱት ቁጥር የማነቃቃት ሀይሉ ይበልጥ የሚጨምር ነው፡፡
4. ውሃ
ውሃ የምግብ ክፍል ውስጥ ይመደባል ብለው የሚከራከሩ ምሁራን ዛሬም ድረስ ምክንያታቸውን በጥበብ ሲያስቀምጡ ይስተዋላሉ፡፡ የስፖርት ሳይንስ ምሁራንም በቀን ውስጥ ብዙ ውሃ መውሰድ ለሰውነታችን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አበክረው የሚገልፁት እውነት ነው፡፡
ወደ ዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ልመልሳችሁና፣ ውሃ ለማነቃቃትም እንደመፍትሄ የሚወሰድ ሆኗል፡፡ መቼም ፅሑፌን ያስተዋለ የዱር ተማሪ ጥናት ለማጥናት ሲል እግሩን በቀዝቃዛ ውሃ የሚዘፍቅበት ሁኔታ አዕምሮው ላይ ደቅን ሊልበት ይችላል፡፡ ምሁራን የሚሉት ግን ከእንቅልፍ በፊት አንድ ብርጭቆ ውሃ ጠጥቶ መተኛተ በጧት ያለችግር ለመንቃት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው፡፡ በተጨማሪም ማታ ላይ በሙቅ ውሃ ሰውነታቸውን ተለቅልቀው የመተኛት ልምድ ያላቸው ሰዎች ወደ ስራቸው በጠዋት ለመውጣት ንቁ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
5. ምግብ
አባቶች የጠዋት ምግብ የሰውነት ምሰሶ ነው ይላሉ፡፡ ሳይንሱም ለአበው አባባል ማረጋገጫውን ከሰጠ አያሌ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ በዘርፉ የተፃፉ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በጠዋት ጥሩ ምግብ የመመገብ ልምድ ያለው ሰው ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ንቁ ይሆናል፡፡ ምሁራኑ ለዚህ ማስረጃነት የሚያቀርቡት የሰው ልጅ በሚርበው ጊዜ መላ ሰውነቱ የመዳከም ስሜት የሚጫጫነው ሲሆን ጥሩ ምግብ ሲያገኝ ግን መላ አካሉ ይበረታታል›› በማለት ነው፡፡
ምሳና ራት ላይ የምንመገባቸው ምግቦች ጣፋጭ መአዛ ያላቸው፣ ከሩቁ የሚጣሩ ከሆነም በአፍንጫችን የሚገባው የምግብ ሽታ ሰውነታችንን የማነቃቃት ሃይል ይኖረዋል፡፡ አትክልትና ፍራፍሬዎችም ለንቁነት ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሲሆን ዓሣና እንቁላልም ተከታዩን ዳራ የሚይዙ የምግብ አይነቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ቀድሞውንስ ጆንያም በእህል ይቆማል አይደል የሚባለው፡፡
6. ቸኮሌት
እርግጥ ቸኮሌት ከፍተኛ የሆነ ስብ ስላለው አብዝቶ መጠቀሙ አይመከርም፡፡ ነገር ግን ለንቃት ይረዳ ዘንድ ቡና በሌለበት አጋጣሚ፣ ቸኮሌትን እንደ አማራጭ ማነቃቂያ መጠቀሙ ምሁራንንም የሚያስማማ ሀቅ ሆኗል፡፡ እንደ ባለሞያዎች ገለፃ፣ ቸኮሌት ስንወሰድ በውስጣችን ከፍተኛ የሆነ የመነቃቃት እና የመመሰጥ ዝንባሌ የሚከሰት ሲሆን ይህም በቀጣይ ለመስራት ባቀድነው ተግባር ላይ በንቃት እንድንከውን ይረዳናል፡፡ ይሁን እንጂ በቸኮሌት የመነቃቃት ሂደቱ ለተወሰነ ጊዜ ስለሚሆን ሌላ የቸኮሌትን ንጥረ ነገር ያካተቱ መጠጦች መጠቀሙ ግድ ሊል ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ ቸኮሌትን መጠቀም የስርዓተ ልመትን ሂደት ከማሳለጥ ባለፈ ለዕድገት እና ለተስተካከለ የአዕምሮ ተግባርም ወሳኝ ነው፡፡
Zehabesha.com