Quantcast
Channel: ጤና – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

በኢትዮጵያ በካንሰር የሚያዙ ህፃናትና አዋቂዎች ቁጥር ለምን ጨመረ?

$
0
0

ካንሰር ከ100 በላይ የሚሆኑ በሽታዎች የጋራ መጠሪያ ሲሆን በሰውነት ውስጥ አንዱ ሴል ብቻውን ሲስፋፋ የሚመጣም ችግር ነው፡፡ ለዓመታት በኢኮኖሚ ረገድ ዕድገት ያሳዩ ሀገራት ችግር ብቻ ተደርጎ ሲቆጠር የቆየው ካንሰር፣ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛና መካከለኛ የዕድገት ደረጃ ባላቸው ሀገራትም ዋነኛው የጤና እክል ሆኖ ቀጥሏል፡፡
Cancer
እናም በኢትዮጵያ በካንሰርና ተያያዥ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ በሆነ መልኩ መጨመሩን የፌዴራል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ እንደተናገረው በየዓመቱ ከ60 ሺ በላይ ዜጎች የካንሰር ተጠቂ እየሆኑ ይገኛል፡፡ በመጪዎቹ 10 ዓመታትም ማለትም በ2025 አሃዙ ወደ 100 ሺ የማደግ ስጋት ጥሏል ብለዋል፡፡ በሁሉም የካንሰር አይነቶች በኢትዮጵያ 45 ሺ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ነው የሚገመተው፡፡ በተለይ በገዳይነታቸው በቀዳሚነት የሚቀመጡት የጡትና የማህፀን በር ካንሰር ብቻቸውን፣ ከ12 ሺ በላይ ዜጎቻችንን ህይወት በየዓመቱ ይቀጥፋሉ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በዜጎች ላይ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች የጡት፣ የማህፀን በር ጫፍ፣ የሽንት ፊኛ መግቢያ ካንሰርና የአንጀት ካንሰር እንደ አደገኝነት ደረጃቸው ተዘርዝረዋል፡፡ ከፕሮስቴት ካንሰር ውጪ ባሉት ሶስቱ የካንሰር አይነቶች ሴቶች በይበልጥ እንደሚጠቁ ነው መረጃዎች የሚናገሩት፡፡ በዚህ መሰረት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በካንሰር የመያዝ ዕድላቸው 67 በመቶ እንደደረሰ ጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል በሂውማን ፓፒሎማ (HPV) ቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፈው የፕሮስቴት ካንሰርም በርካታ ወንዶችን ለሞት እያበቃ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በአንፃሩ እንደ ሌሎች ሀገራት የትንባሆ አጫሾች ቁጥር፣ በኢትዮጵያ ከ20 በመቶ የማይበልጥ መሆኑን ተከትሎ በሳንባና ተያያዥ የሰውነት አካላት ላይ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች ዝቅተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ ነገር ግን ይሄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለካንሰር በሽተኞች ሞት የ20 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለሞት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል ካንሰር የ40 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

በ2030 ደግሞ የመሪነት ድርሻውን እንደሚይዝ ተጠብቋል፡፡ ያም ቢሆን ብዙዎቹ የካንሰር በሽታዎች ሊታከሙና ፈውስ ሊገኝላቸው የሚችሉ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የሆነውም የካንሰር ስጋት ያላቸው ሰዎች፣ በጊዜ ወደ ጤና ተቋም አለመምጣታቸውና ተገቢውን የባለሙያ እርዳታ አለማግኘታቸው ይገለፃል፡፡

በሀገራችን ለ90 ሚሊዮን ሕዝብ የካንሰር በሽታ ህክምና የሚሰጠው፣ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡ ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞች ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡትም ህክምና ለማግኘት ቢያንስ የአንድ ዓመት ቀጠሮ መጠበቅ አለባቸው፡፡ የዚህን ችግር መኖር የሚያረጋግጡት ዶ/ር ኩኑዝ፣ ከበሽታው ባህሪ አንፃር ጊዜ ሲሰጠው፣ በሰውነት ውስጥ ለማሰራጨት ዕድል የሚያገኝ በመሆኑ ሁኔታው አሳሳቢ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
በካንሰር ህክምና ስፔሻላይዝድ አድርገው፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ሲሰጡ ከነበሩ አራት ባለሙያዎች መካከል አንዱ በጡረታ መገለላቸውን ተከትሎ፣ በቀሪዎቹ ሶስት ዶክተሮች ብቻ የካንሰር/የጨረር ህክምና ይሰጣል፡፡ የህክምና መሳሪያው ውድነትም አገልግሎቱን በማዳረስ ረገድ ፈተና መፍጠሩን ዶ/ር ኩኑዝ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የካንሰር በሽታ ህክምናን ፍለጋ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚመጡና የገንዘብ አቅሙ ኖሯቸው ማረፊያ ያላገኙ ሰዎች በየኮሪደሩ ለመተኛትና ወረፋቸውን ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ አንድ ለእናቱ የሆነው የጤና ተቋም/ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል/ ከአቅሙ በላይ ከሆነው ችግር ጋር እየታገለ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን በሽታው በየዕለቱ በውስጣቸው እየተሰራጨና እያዳከማቸው ተራቸውን የሚጠባበቁት ዜጎችም ተስፋ ብቻ ይመስላል ስንቃቸው፡፡

እ.ኤ.አ  በ2012 ብቻ በዓለም 14 ሚሊዮን ሰዎች አዳዲስ የካንሰር ተጠቂዎች ሆነው ሲመዘገቡ፣ በተመሳሳይ ዓት 8.2 ሚሊየኖች ደግሞ በዚህ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አስርት ዓመታትም ይሄ መጠን በ70 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ በካንሰር ሳቢያ ለሚከሰቱ ምቶች አምስቱ ተጠያቂ ምክንያቶችን ዘርዝሯል፡፡ እነርሱም ከፍተኛ ክብደት፣ ዝቅተኛ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢነት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስና አልኮል ማዘውተር እንደሆኑ አስቀምጧል፡፡

በኢትዮጰያ የህፃናት ካንሰር በሽታ ለምን ጨመረ?

በኢትዮጵያ የካንሰር በሽታ ጭማሪ ለማሳየቱ የተወሰኑ ምክንያቶችን ይዘረዘራሉ፡፡ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦች መበርከት፣ ኢንፌክሽን (በተለይ ከHPV ጋር በተገናኘ) የአካል ብቃት አለማድረግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እንዲሁም በሽታው ዕድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ተጠቅሷል፡፡ በህፃናት ላይ የሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች በአዋቂዎች ላይ ከሚከሰቱት አንፃር የተለዩ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ የደም ካንሰር፣ የዕጢ ካንሰርና የአጥንት ካንሰር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የካንሰር አይነቶች በህፃናት ላይ ያለመከሰት ዕድል ቢኖራቸውም አልፎ አልፎ ተከስተው ይታያሉ፡፡

የአጥንትና የደም ካንሰር የሆነው ሉኪሚያ/Leukemia/ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በህፃናት ላይ የመከሰት ዕድሉ 30 በመቶ ሆኗል፡፡ በሽታው በፍጥነት የመሰራጨትና በህመምተኛው ላይ ድካም፣ መድማት፣ ክብደት መቀነስ፣ የአጥንት ህመምና ሌሎች ምልክቶች አሉት፡፡ በሽታው መኖሩ እንደታወቀም በአፋጣኝ የኬሞቴራፒ ህክምናን መከታተል መጀመር እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ የደምና የአጥንት ውስጥ ካንሰር የሆነው ሉኪሚያ ደግሞ በኢትዮጵያ የህፃናቱ ዋናው የጤና እክል ነው፡፡

በመሆኑም በዚህ በሽታ ተይዘው የሚመጡ የህፃናት ቁጥር መጨመሩን ነው የተነገረው፡፡ ዶ/ሮች እንደሚሉት ‹‹ወላጆች በህፃናት አመጋገብ ላይ ትኩረት እስካላደረጉ ድረስ በአሳሳቢነቱ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ትኩስና አዳዲስ የሆኑ ምግቦችን ከመመገብ ይልቅ፣ የታሸጉ መጠጦችንና ምግቦችን ማስለመዳቸው ለካንሰር መስፋፋት ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡

በህይወት ዘመናቸው ከሶስት ሴቶች አንዷና ከአምስት ወንዶች አንዱ በካንሰር የመያዝ ዕድል እንዳላቸው አለምአቀፍ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ወንዶችን በብዛት የሚያጠቁና ወዲያው ቢታወቁ ለመክሰም የሚችሉ የካንሰር አይነቶችን እንዲመረመሩ ይመክራል፡፡ በተለይም ወንዶች ከ50 ዓመት በኋላ፣ ሴቶች ከ35 ዓት ዕድሜ በኋላ የካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ወንዶችን በተመለከተ የሳንባ ካንሰር፣ የትልቁ አንጀት ካንሰርና ፕሮስቴት ካንሰር ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ ሴቶችን በተመለከተ ደግሞ የጡት ካንሰር፣ የማህፀን በር ካንሰር፣ የሳንባ ካንሰር፣ የትልቁ አንጀት ካንሰር፣ የማህፀን ጋን ካንሰር፣ የዕንቁላል ዕጢ (ኢቫሪያን) ካንሰርና የቆዳ ካንሰር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>