Quantcast
Channel: ጤና – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Health: ሙሉ ጨረቃና እብደት፣ ራስን ማጥፋትና የእንቅልፍ እጦት ምን አገናኛቸው?

$
0
0

የእኛ ምላሽ!
በጠፍ ጨረቃ ደጃፌ ላይ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ቤት መግባት ያሰኘኝ አይመስለኝም፡፡ ብቻ የጨረቃዋ ድምቀት ፍጥጥ አድርጎኝ ቁጭ ብያለሁ፡፡ እንቅልፍ ያስፈለገኝ አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ደግሞ ጥሎብኝ ነው መሰል፣ ከዋክብትንና ጨረቃን ለስለስ ባለ ነፋሻ አየር መታደም እጅግ ሐሴትን ይሰጠኛል፡፡ ዛሬ ግን በጠራው ድቅድቅ ጨለማ ወለል ብላ የምትታየኝ የኛዋ ብቸኛዋ ጨረቃ ናት፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ርቀት እነ ኔቡላን የመሰሉ የሰማዩ ግርማዎች ሲንቦገቦጉ ይታዩኛል፡፡ በዚህ ትዕይንት መሀል ግን ትኩረቴን ስቦት እያነበብኩት ያለ ነገር አለ፡፡ ጆርናል ኦፍ ሳይካትሪ ሰርቪስስ፣ በመድረ አሜሪካ የሳይንሳዊ ጥናት ጆርናል፡፡ ከዚህ ጆርናል ላይ አንድ ትኩረቴን የሳበ ጥናት ይገኛል፡፡ በጨረቃና በሰው ልጅ መካከል ያለ ጥብቅ ቁርኝት፡፡ ወደድንም ጠላንም ጨረቃ በእኛ ላይ የማይካድ ተፅዕኖ አላት ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ነገሮችን አስፍሯል፡፡
ask your doctor zehabesha

እርግጠኛ ነኝ፣ ብዙዎቻችን በተለይም የሆሊውድ ፊልም ያየን ሰዎች በአስፈሪና አስደንጋጭ ዘውግ ፊልሞቻቸው፣ ጨረቃና የሰው ልጅ ምትሃታዊ ለውጦችን በብዛት አይነት ይሆናል፡፡ ነገሩ ከፊልምነት የዘለለ ነገር የለውም ብለንን እናልፍ ሆናል፡፡ ሆኖም ግን ትንሽ ቢሆን አሊያም እንደ ፊልሙ የተጋነነ ባይሆንም ጨረቃና እኛን የሚያቆራኙን፣ ብዙ ጉዳዮች መኖራቸው እውነትነት አለው የሚሉ ወገኖች መኖቸው እሙን ነው፡፡

ጨረቃና አደጋዎቿ

ብታምኑም ባታምኑም ሙሉ ጨረቃ በምትውልበት ወቅት፣ ሰዎች እንቅልፍ በአግባቡ ለመተኛት ያቅታቸዋል ይለናል ጆርናል ኦፍ አፌክቲቭ ዲስ ኦርደርስ በ1999 ላይ ደረስኩበት ባለው ጥናት፡፡ አስገራሚው ቁም ነገር ደግሞ ለዚህ ምክንያት ነው ብሎ ያስቀመጠው ትንታኔ፣ የፊዚክስ እውነታዎች ላይ ተመርኩዞ መሆኑ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ምድር ላይ ያሉ የውሃማ አካላትን ወጀብ (ማዕበል) የሚፈጥሩት ፀሐይና ጨረቃ ናቸው፡፡ ይህ የወጀብ እንቅስቃሴም ወደ ጨረቃ አቅጣጫ ያለ ውሃማ አካልን በስበት ኃይል ወደ ጨረቃ ስለሚጎትት፣ ወጀቡ ይፈጠራል ወደ ፀሐይ አቅጣጫ ያለውም ውሃማ አካል እንዲሁ ወደ ፀሐይ ይሳባል፤ ይህም (ታይዳል ዌቭ) በአማርኛችን ስንመልሰው ወጀብ ይፈጠራል፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ አካል 75 በመቶው ውሃ በመሆኑ፣ ሙሉ ጨረቃ በሚሆንበት ወቅት ይኸው የስበት ኃይል ተፅዕኖ ሳይፈጠርብን እንደማይቀር ይገመታሉ፡፡

በምድረ አሜሪካ 11940 የደረሱ አደጋዎች ላይ ያተኮረ ጥናት፣ በኮሎራዶ ቬቴሪናሪ ሜዲካል ሴንተር ተመራማሪዎች ሲያካሂዱ፣ ደረስንበት ያሉት መረጃ እንደሚያሳየው ዘወትር ከሚደርሰው ውድመቶች ላይ 23 በመቶ የመጎዳዳት አደጋ በዚህ የሙሉ ጨረቃ ወቅት ደርሷል፡፡

የአሜሪካ አብስቴትሪክስና ጋይናኮሎጂ ጆርናል ጥናት ደግሞ፣ በሴቶች የወር አበባ ላይ አተኩሮ በሙሉ ጨረቃ ወቅት ያለውን ሁኔታ ከተለመዶው ምሽት ጋር አነፃፅሮ አጥንቷል፡፡ በእርግጥ የሴቶች የወር አበባ አመጣጥ በራሱ የሚለያይና ቋሚ ሂደት የሌለው የተፈጥሮ ክስተት ነው፡፡ ክስተቱም በየ28 ቀናት ውስጥ የሚከሰትና ከእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ በአንዱ ሊመጣ የሚችል ቢሆንም፣ በሙሉ ጨረቃ ዕለት ግን በ29 እና 30 ቀናት ውስጥ መከሰቱ፣ ይህም የተከሰተባቸው 60 በመቶ የሚሆኑት ጥናት የተካሄደባቸው ሴቶች መሆናቸው ነው፡፡

ሙሉ ጨረቃ ስትሆን ራስ ህመም ይበረታል፣ እንቅልፍ ቶሎ አይመጣም አንዳንዶችንም ታሳብዳለች?

ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ወቅት፣ አንዳንድ ግለሰቦች ሊያብዱ ይችላሉ የሚለውን የቆየ እምነት ለመፈተን፣ ቆርጠው ከተነሱ ተመራማሪዎች መካከል የፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲው፣ ጀምስ ሮትንና የሳስካችዌን ዩኒቨርሲቲው ኢቫን ኬሊ ናቸው፡፡ በ37 ተመሳሳይ ጥናቶች ላይ ተመርኩዘው ለረጅም ጊዜ ጉዳዩን መረመሩት፡፡ የአእምሮ ህመምተኞች ሆስፒታሎችንም ሁኔታ አጠኑ፡፡ ነገር ግን ሰዎች እንደሚያስቡት፣ ጨረቃ ያን ያህል ለእብደግ አታደርስም አልያም ተጋንኖ የሚታየን በጨረቃ ወቅት ነው እንጂ፣ በሌላ ጊዜያትም ሰዎች በተመሳሳይ ቁጥር እንደሚያብዱ ጥናታቸው ይጠቁማል፡፡ ራስ ህመምንም ቢሆን የተለየ ራስ ህመም ምልክቶችን በዚህ ወቅት እንዳላዩ ጥናታቸው ይናገራል፡፡ ሰዎች ቀደም ሲሉ ሙሉ ጨረቃ ስትውል ችግሩ እንደሚባባስ ስለሚያስቡ፣ በሙሉ ጨረቃ ዕለት ችግሩ እንደተከሰተባቸው አድርገው ስለሚያስቡ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ያምናሉ፡፡

እንቅልፍ እጦትን በተመለከተ ግን ሙሉ ጨረቃ በምትውልበት ወቅት ሰዎች ቶሎ እንደማይተኙ ጥናታቸው ያትታል፡፡ እንደነ ጀምስ ሮተን እምነት ይህ ሊሆን የሚችለው፣ የጨረቃዋ ረጅም ሰዓት ደምቃ መታየት ሰዎች ቶሎ እንዳይተኙ የሚመች ሁኔታዎችን ስለምትፈጥር ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ እናም ሰዎች በነፋሻ አየርና በደማቅ የጨረቃ ብርሃን ታግዘው፣ እንቅልፋቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደሚያርቁት ይታሰባልም፡፡

ሁለት ጥናቶች እርስ በእርሳቸው እንዳይስማሙ ያደረገ ክስተት ደግሞ በእንስሳቶች ላይ የሚታየው ሁኔታ ነው፡፡ በእንግሊዝ የተደረገ አንድ ጥናት በ2001 ላይ በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ላይ ለህትመት ሲበቃ፣ ውሾች በሙሉ በጨረቃ ወቅት ሰዎች ላይ ከባድ አደጋ ያደርሳሉ፡፡ ውሾች ቀዳሚዎች ሆነው በጥናቱ ላይ ተመዝግበዋልም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአውስትራሊያ የተደረገ ጥናት በዚሁ ጆርናል ላይ ታት እንደሚነበበው፣ ውሾች በማንኛውም ምሽ ሰዎች ላይ ጉዳት የማድረስ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ በመረጃ የተደገፈ ነገር አሳይቷል፡፡ ይህ ጥናት እንደሚያምነው፣ ውሾች ምሽት ከሆነ በማንኛውም ወቅት አደጋ የማድረስ እድላቸው ከቀን ይበልጣል፡፡ በመሆኑም የውሾች አደጋ ከጨረቃ ጋር ምንም እንደማያያይዘው ጥናቱ ይደመድማል፡፡

በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቆየት ያሉና ጥናታዊ ግምቶች መካከል፣ ጨረቃና እብደትን የሚያይዙ አመለካከቶች ናቸው፡፡ ከ2004 ጀምሮ በምድረ ካናዳ ጥናት ያካሄዱ ሳይንቲስቶች፣ በጆርናል ኦፍ ኢፔሌፕሲና ቢሄቪየር ላይ እንዳሰፈሩት ሰዎች እንደሚያምኑት፣ ሙሉ ጨረቃ በምትውልበት ወቅት ምንም አይነት የተለየ የአዕምሮ ችግር እንደሌለ እና ጥናታቸውም የሚፈራውን ነገር ማግኘት እንዳልቻለ ያትታል፡፡

አሜሪካዊው የሳይንስ ጋዜጠኛና የባድ ሳይንስ አምደኛ፣ ‹‹ፖሊሶችም ሆኑ ነዋሪው በሙሉ ጨረቃ ወቅት ከባድ አደጋ ይደርሳል አልያም ያጋጥመናል ብለው ካመኑ ብዙ ችግሮችና አደጋዎች ከወትሮው በተለየ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ሙሉ ጨረቃ ስለዋለች ሳይሆን፣ ሰዎች አመለካከታችን ውሏችንን ስለሚፈጥረው ነው፡፡ የምናስበው ነገር የምንፈልገውን ክስተት ተፅዕኖ ውስጥ ያሳድረዋል…›› ይላል፡፡

እውነቱ ወዴት ይሆን?

ሳይንስ እርስ በእርሱ መስማማት ያልቻለበት ጉዳይ ይመስላል፡፡ በተለይም እንቅልፍ ላይ ሙሉ ጨረቃ በምትውልበት ምሽት፣ ተፅዕኖ እንዳለው የሚያምኑ ሳይንቲስቶች መኖራቸውና በተቃራኒው ደግሞ፣ ይህን የሚቃወሙና ከጨረቃ ጋር ምንም የሚያያይዘው ጉዳይ እንደሌለ የሚጠቁሙ ሳይንቲስቶች በሌላኛው ወገን ሆነው እሰጥ አገባቸውን የቀጠሉ ይመስላል፡፡

አብዛኞቹ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ የመረጃ አሰባሰባቸው ተቀራራቢ በመሆኑ ደግሞ ጉዳዩን እንቆቅልሽ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ግን አብዛኞቹ ተመማሪዎች ጠንከር ያለው አመለካከቶች ላይ አንድ አቋም ያላቸው ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሌላው ጊዜ በተለየ ለአዕምሮ ህመም የሚጋለጡ ሰዎች፣ ሙሉ ጨረቃ ወቅት ያብዳሉ አልያም አቅላቸውን ስተው፣ ጨርቃቸውን ጥለው ጎዳና ይወጣሉ የሚባለው የቆየ አመለካት እውነት እንዳልሆና፣ እስካሁን ድረስ ሳይንስ ይህን ነገር ባያረጋግጥም እውነት የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ወደፊትም ጥናቶች የዚህ አመለካከትን እውነትነት አልያም ውሸትነት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ነገር ግን ትልቁ ጉዳይና ብዙዎቹን ሳይንቲቶች አላግባብ ያለው አመለካከት ሙሉ ጨረቃና የሰዎች እንቅልፍ ዑደት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይም ሳይንቲስቶች ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ እንቆቅልሽ የሆነው ጉዳይ ደግሞ፣ ሁለቱም ጎራዎች የተለያዩ ጥናቶችን አድርገው ደረስንበት ያሉት ውጤት ተቃራኒ የማያስማማ መሆኑ ነው፡፡

ሆኖም የሰሞነኛ ጨረቃችን፣ የበልግ ዝናባችን እንደቀረ ምልክት መሆኑን ደግሞ የተለያዩ የስፔስ ሳይንስ፣ የአየር ንብረት ጥናቶችን ተመርኩዘን መገመት እንችላለን፡፡ በእርግጥም ዘንድሮ የበልግ ዝናብ፣ በብዙዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም ሙሉ ጨረቃ በታየችባቸው አካባቢዎች አለመኖሩ እሙን ነው፡፡
መቼም ይቺ ሙሉ ጨረቃ የማታመጣብን የለምና፣ ከዝናብ እጥረት አልፎም ጤናችን ላይ ታሳድራለች የተባለው ተፅዕኖም እውነት ይሆን? በእርግጥ ጨረቃ የሰውን ልጅ የማሳበድ አቅም ይኖት ይሆን? ሰዎችንስ እንቅልፍ የምትነሳበት ወቅት አላት ይሆን? ጊዜና ሳይንስ ይፍቱት እላለሁ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 384

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>