ሰዎች ስፖርት እየሰሩ ራሳቸውን ስተው ስለምን ይወድቃሉ?
እንቅስቃሴ የሚያደርጉና የተስተካከለ አካላዊ ቁመና ያላቸው ሰዎች፣ ከልብ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ በሽታዎችና ለሞት የመጋለጥ ዕድላቸው በተቃራኒው ካሉት አንፃር እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በእንቅስቃሴ ወቅት ከሚመጣ አደጋና ሞት ሙሉ ለሙሉ የተጠበቁ አለመሆናቸው ነው፣ ዘ ሳይንስ ኦፍ ስፖርት ባሰፈረው ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያስረዳው፡፡
ስፖርተኞች በምንልበት ጊዜ የግድ በአትሌቲክስ በሩጫና ውርወራ እንዲሁም በእግር ኳስና በቦክስ ጨዋታዎች ውስጥ የሚሳተፉትን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ክብደት ለመቀነስ ወይም የኮሌስትሮል መጠንን ለማስተካከል አልያም የደም ውስጥ ደም ግፊትንና የስኳር መጠንን ለማስተካከል ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽት ወይም በሐኪም ትዕዛዝ ዕለታዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ይሰራሉ፡፡ በተለይ የልብ ፍጥነትን የሚጨምሩ ስፖርቶች በየዕለቱ ወይም ከአንድ ሰዓት በላይ በተሰሩ ቁጥር እንዲህ መሰል ሰዎችን በድንገተኛ ለሚጥሉ ወይም ለሚገድሉ ህመሞች ይጋለጣሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የዘርፉ ባለሙያዎች ስፖርተኞችን በድንገት ሊጥሉ ወይም ሊገድሉ ይችላሉ የሚሏቸው ህመሞች ውስጥበዋናነት ከልብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የጡንቻ መጠን መተለቅ ችግር ወይም በህክምና ቋንቋው ‹‹Hypertrophic cardiomyopathy›› አንዱ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ደምን ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚረጨው የግራው የታችኛው ልብ ክፍል ጡንቻ በወፈረ ቁጥር ድንገት ደም መርጨትን ሳይታሰብ በመግታት አንድን ሰው በድንገት ጠብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከልብ ጋር የተያያዘው ሁለተኛ ገዳይ ደግሞ በማህፀን ውስጥ አንድ ፅንስ የተለያዩ አካላቶችን ሲያዘጋጅ የአፈጣጠር ዝግጅት ሊከሰት በመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በልብ አፈጣጠር ወቅት የሚከሰት ዝንፈት ‹‹Congenital malformation›› ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እንዲሁም ልባችን ኤሌክትሪካዊ የአሰራር ፍሰት ያለው ሲሆን በሆነ አጋጣሚ ይህ መሰሉ የኤሌክትሪክ ፍሰት እክል ‹‹Electrical abnormalities of the heart›› ሌላው ለድንገተኛ ሞት የሚያጋልጥ ነው፡፡ የልብ ምት መዛባት ማለትም ከወትሮ የልብ ፍጥነት በላይ ወይም ከወትሮው የልብ ፍጥነት በታች አልያም የልብ ፍጥነት መጨመርና ወጥነት ማጣት በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡
ከልብ ችግር ወጣ ስንልም በተለይ አስም በመባል የሚጠራው የመተንፈሻ አካል ህመም ያለበት አንድ ሰው በድንገት የአየር ቧንቧው በመጥበቡ ትንፋሽ ሊያጥረውና ሊሞት የሚችል በመሆኑ እንዲህ መሰል ችግር ያለባቸው ሰዎች ስፖርት ከመስራታቸው በፊት ሐኪማቸውን ቢያማክሩ ወይም እንደ ቬንቶሊን አይነት የአየር ቧንቧ ማስፊያ መድሃኒቶችን ቢይዙ መልካም እንደሆነ ይጠቆማል፡፡
የስኳር ህመም ሌላኛው በድንገት ራስን ለመሳት የሚያጋልጥ ህመም ነው፡፡ በዚህ ረገድ የደም ውስጥ ግሉኮስ መውረድ ወይም ከልክ በላይ መውጣት አንድን የስኳር ህመምተኛ ራሱን ስቶ እንዲወድቅ ወይም ደግሞ በድንገት እንዲሞት ሊያደርገው የሚችል በመሆኑ የስኳር ህሙማን በተቻለ መጠን ከሐኪማቸው ጋር በመወያየት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን መስራት ወይም ከስፖርት በፊትና በኋላ የደም ውስጥ ግሉኮስን በመለካት በጣም ካነሰ ተጨማሪ ካሎሪ የመውሰድና ከጨመረ ደግሞ ስኳር አውራጅ ኢንሱሊን (መድሃኒት) መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በስፖርት ጊዜ የደም ግሉኮስ መመርመሪያ፣ ጣፋጭ ምግብ፣ እንዲሁም ኢንሱሊን መያዝና የስኳር ህመምተኝነትን የሚገልፅ ምልክት በእጅ ላይ ማሰር ወይም መታወቂያ ካርድ መያዝ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
‹‹Heat Stroke›› በመባል የሚጠራው ችግር ደግሞ ሙቀትን ተከትሎ በሚመጣ ላብ ሳቢያ አንድ ሰው ራሱን ሊስት ይችላል፡፡ ከፍተኛ ፈሳሽ በላብ መልክ ሲወጣ በሚጠጣ ውሃ ወይም ማዕድን በሚተኩ መጠጦች የሚተካ ባልሆነ ቁጥር ይህ መሰል ችግር ሊከሰት ይችላልና ነገሩን ከዚህም አንፃር ማጤን መልካም ነው፡፡ ከደም ግፊት ጋር የተያያዘ ስትሮክም እንዲሁ በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስን የሚያስከትል በመሆኑ የደም ግፊት ህሙማን ሐኪማቸውን ያማክሩ፡፡
እንደሚታወቀው ስፖርተኞች በውድድር አልያም በልምምድ ላይ ሳሉ በድንገት ሲሞቱ፣ የሚዲያዎችና በአጠቃላይ የዓለማችን ዋና ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መነጋገሪያነቱ ከፍ ይላል፡፡ ፍጥነትና ጉልበት በሚፈልጉ የሜዳ እና የጎዳና ላይ ስፖርታዊ ውድድሮች ከፍተኛ ስም ያተረፉ ስፖተኞች በድንገት ህይወታቸው አልፏል፡፡
በእንቅስቃሴ ላይ ሳሉ በድንገት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች፣ ስር የሰደደ የልብ ችግር እንዳለባቸው ቀድመው ምንም አይነት መረጃ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በእንቅስቃሴ ወቅት ከልብ ችግሮች አይነቶች ጋር የተያያዙ በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ የእነዚህ በሽታዎች በአትሌቶች ላይ በድንገት የመከሰት ዕድላቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ጥናቶች ችግሩ ከ10 ሺ ወይም ከ20 ሺ አትሌቶች በአንዱ ላይ ሊከሰት እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡ ነገር ግን አሃዙ ስፖርትን በሚያዘወትሩ፣ ያለ ቅድመ ዝግጅት ስፖት በሚጀምሩበት እንዲሁም ወጣ ገባ በሚሉት ላይ እጅጉን ከፍ ይላል፡፡
በየዕለቱ የሚደረግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልባችንን በሚገባ ይጠብቅልናል፣ የተመታጠነ ኮሌስትሮል በሰውነታችን ውስጥ እንዲኖር፣ ልባችን ስራውን እንዲያቀላጥፍ እንዲሁም ህይወታችን የተሻለ እንዲሆንና ዕድሜአችንን ለመጨመር የማይተካ ሚና አለው፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በራሱ እጅግ ጠቃሚ እንጂ አደገኛ አይደለም፣ ጥቅሞቹም በፍፁም መዘንጋት እንደሌለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
በድንገተኛ ሞት ላይ የሚወጡ ጥናቶች፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት ለሚከሰተው ድንገተኛ ሞት፣ እንቅስቃሴ በራሱ ተጠያቂ ነው አልያም ሌሎችም ምክንያት ይኖራሉ ሲሉ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ሳይታሰብ ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቀደም ሲል የሚያውቁት ወይም የማያውቁት በተለይ የልብ ችግር ዋነኛው ምክንያታቸው ሊሆን እንደሚችል አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡ ሌሎች መረጃዎች መካከለኛ እንቅስቃሴ ለድንገተኛ ሞት ምክንያትነቱ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በአንፃሩ ማራቶንና ሀገር አቋራጭ ሩጫዎች ደግሞ ከ5-7 እጥፍ አደጋውን ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡ የቀድሞው ዝነኛ የማራቶን ሯጭ አልቤርቶ ሳላዛር፣ በልብ ድካም ሳቢያ በልምምድ ላይ ሳለ ህይወቱ ያለፈ ታላቅ አትሌት ነው፡፡
በስፔን ላሊጋ (የእግርኳስ ውድድር)፣ በፕሮፌሽናልነት ደረጃ ሲጫወት የነበረው የ22 ዓመቱ፣ አንቶኒዩ ፑየርታ ጨዋታ ላይ ራሱን ስቶ በመውደቁ ህይወቱን አጥቷል፡፡ ክስተቱ መላውን የዓለም የእግርኳስ ተመልካች ሐዘን ውስጥ የጣለ ሆኖ አልፏል፡፡ ሌላው ካሜሮናዊ ኢንተርናሽል ቪቪየን ፎዬ በሜዳ ላይ በድንገት ተዝለፍልፎ በመውደቁ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም፣ ልቡ መስራት አቁማለችና የትኛውም የህክምና ባለሙያ ህይወቱን ሊታደጋት ያልቻለ እግርኳስ ተጨዋች ነበረ፡፡ የዝነኛው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የቀድሞ ባለቤትም እንዲሁ በልምምድ ላይ ሳለች በድንገት ህይወቷ ያለፈች ሌላኛዋ አትሌት ናት፡፡
እነዚህን ጨምሮ የአንድ ወቅት መነጋገሪያ የነበሩ የስፖርተኞችን የሜዳ ላይ ሞት ሰምተናል፣ ነገር ግን ማናችንም ይሄ ተከስቷል ብለን ስፖርትን ከማዘውተር አላገደንም፡፡ በእርግጥ ክስተቱ በእኛ ላይ የመፈጠር ዕድላቸውን በማጤን ለጥንቃቄ እንደመነሻ አገልግለውን ይሆናል፡፡
እግርኳስን ጨምሮ፣ የዓለማችን ትልልቅ የስፖርት ክለቦች ለሚገዟቸው ስፖርተኞች ጤንነት ትልቅ አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡ የልብ አልያም ሌላ መሰረታዊ የጤና ችግር ጋር የሚገኝን ስፖርተኛ አያስተናግዱም፣ ወይም እጅግ ጉልበትና ፍጥነት በሚጠይቅ የውድድር መድረክ ላይ እንዲወክላቸው ዕድል አይሰጡም፡፡ በዚህም ስፖርተኞች ሙሉ የጤና ምርመራን እንዲያልፉ ያስገድዳሉ፡፡ በተለይ በአውሮፓ የእግርኳስ ሊጎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ድንገተኛ የስፖርተኞችን ሞት የማንመለከተውም፣ በጤና ምርምር ላይ ያላቸው ጥብቅ አቋም ነው፡፡
በእንቅስቃሴ ወቅት ሊኖር የሚችልን ድንገተኛ ሞት በምን መልክ ልናስወግድ እንችላለን?
1. ትምህርት፡- ስለልብም ሆነ በእንቅስቃሴ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በተመለከተ፣ ራስን ለመረጃ ማብቃት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ አደገኛው ክስተት ከመፈጠሩ በፊት በሰውነታችን ላይ የተለያዩ ምልክቶችን ልንመለከት እንችላለን፡፡ በተለይ ራስን መሳት፣ የአተነፋፈስ ችግር ወይም የትንፋሽ እጥረት፣ የደረት ላይ ህመምና ድብርት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህንና ሌሎች ምልክቶች በሚገባ መረዳት፣ በእንቅስቃሴ ውስጥ ሳለን ማወቅ የሚገባን ይሆናል፡፡
2. ምርመራ፡- ብዙዎቹ የአደጋው ምልክቶች በቀላሉ የሚደርስባቸው አይደሉም፡፡ ብዙዎች አጠቃላይ የጤና ምርመራ የማድረግን ከፍተኛ ጥቅም ትኩረት አይሰጡም፣ ተጨማሪ ወጪ አድርገውም ይወስዱታል፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ (ለጤና አልያም ለውድድር) ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስንጀምር፣ የልባችንን ጨምሮ፣ የግፊት፣ የስኳር፣ የሳንባና የመላ ሰውነታችን የጤና ሁኔታ በምርመራ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡
3. የቤተሰብን የጤና ታሪክ ማወቅ
ስፖርተኞችም ሆነ እንቅስቃሴን በየዕለቱ መከወን የሚፈልጉ ሰዎች፣ በቅድሚያ ማድረግ ካለባቸው ተግባር መካከል በጤና ዙሪያ የቤተሰቦቻቸውን ታሪክ ማወቅ ነው፡፡ ልብ እና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ችግሮች የቤተሰቦቸው ጉዳይ ከነበሩ፣ የእኛም ችግር የመሆን ዕድል ይኖራቸዋልና ለምርመራ የህክምና ባለሙያ እርዳታ ያስፈልገናል፡፡ (የልብ ችግሮች፣ የስኳርና የደም ግፊት ችግሮች በዘር ይወረሳሉ)
4. ከሚታወቅ ህመም ጋር ወደ እንቅስቃሴ የሚመጡ ሰዎችም፣ ህመማቸው እስከሚፈቅድላቸው ርቀት ድረስ ብቻ መንቀሳቀስ እንዲሁም ቅድመ ሁኔታዎችንም መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡ ከሐኪሞቻቸውም ጋር መመካከራቸውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ ከስኳር ህመም ጋር እያሉ እንቅስቃሴ የሚጀምሩ ሰዎች፣ በበቂ ሁኔታ ምግባቸውንና መድሃኒታቸውን መውሰዳቸውን እርግጠኛ መሆን አለባቸው፡፡
5. ድንገተኛ ራስን መሳት በሚያጋጥም ጊዜ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደተጠበቀ ሆኖ በቦታው የሚደረግ የህይወት አድን ስራም ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ደረትን በመዳፍ ጫን ጫን የማድረግና በአፍ በኩል የሚሰጥ የትንፋሽ እገዛ ግድ ነው፡፡ ግለሰቡ አየር እንዲያገኝ ማድረግ፣ ምላሱ ጉሮሮውን ታጥፎ እንዳይዘጋው ምላስን በጣት መዘርጋትን ማረጋገጥ፣ በፍጥነትም አምቡላንስ መጥራት የሚመከሩ ናቸው፣ መልካም ጤንነት፡፡